ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 31
31
ሕዝቅያስ ያደረገው ተሃድሶ
1ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በዚያ የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው ሁሉን ፈጽመው እስካጠፉአቸው ድረስ ሐውልቶቹን ሰባበሩ፤ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጡ፤ በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኮረብታው መስገጃዎችና መሠዊያዎች አፈረሱ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ።
2ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ያገለግሉም ዘንድ፥ ያመሰግኑም ያከብሩም ዘንድ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አቆመ። 3በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ፥ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፈለውን ወሰነ። 4በእግዚአብሔርም ቤት ለአገልግሎት እንዲጸኑ ለካህናቱና ለሌዋውያን ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ። 5ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን ጠጅ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ ሁሉ በኵራት ሰጡ፤ የሁሉንም አሥራት አብዝተው አቀረቡ። 6በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳም ልጆች የበሬውንና የበጉን አሥራት፥ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን አሥራት አመጡ፤ ከምረውም አኖሩት። 7በሦስተኛው ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ። 8ሕዝቅያስና አለቆቹም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን ባረኩ። 9ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ። 10ከሳዶቅም ወገን የሆነ ዋነኛው ካህን ዓዛርያስ “ሕዝቡ ቍርባኑን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፤ ጠግበናል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ የተረፈውም ይህ ክምር ትልቅ ነው” ብሎ ተናገረ።
የካህናትና የሌዋውያን እንደገና መደራጀት
11ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤት ጎተራ ያዘጋጁ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ። 12ቍርባኑንና አሥራቱን የተቀደሱትንም በእምነት ወደዚያ አገቡት። ሌዋዊውም ኮናንያ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕረግ ሁለተኛ ነበረ፤ 13በንጉሡም በሕዝቅያስና በእግዚአብሔር ቤት አለቃ በዓዛርያስ ትእዛዝ ይሒዒል፥ ዓዛዝያ፥ ናሖት፥ አሣሄል፥ ይሬሞት፥ ዮዛባት፥ ኤሊኤል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስ፥ ከኮናንያና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ። 14የሌዋዊውም የይምና ልጅ የምሥራቁ ደጅ በረኛ ቆሬ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያካፍል ሕዝቡ ለእግዚአብሔር በፈቃድ ባቀረቡት ላይ ተሾመ። 15በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ክፍላቸውን በእምነት ይሰጡ ዘንድ ዔድን፥ ሚንያሚን፥ ኢያሱ፥ ሸማያ፥ አማርያ፥ ሴኬንያ ከእጁ በታች ነበሩ። 16ከሦስትም ዓመት ወደ ላይ ላሉ በየሰሞናቸውም ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፤ 17በየአባቶቻቸውም ቤት ለተቈጠሩ ካህናት፥ ከሀያ ዓመትም ወደ ላይ ላሉ በየሥርዓታቸውና በየሰሞናቸው ለተቈጠሩ ሌዋውያን፥ 18በማኅበሩም ሁሉ በየትውልዳቸው ለተቈጠሩ ለሕፃናቶቻቸውና ለሚስቶቻቸው ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻቸውም ይሰጡ ነበር፤ በእምነት ተቀድሰዋልና። 19በየከተማይቱም ሁሉ በከተማቸው መሰማርያቹ ላሉ ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ ከካህናቱም ወገን ላሉ ወንዶች ሁሉ፥ በትውልዳቸውም ለተቈጠሩ ሌዋውያን ሁሉ ክፍላቸውን ይሰጡ ዘንድ በስማቸው የተጻፉ ሰዎች ነበሩ።
20ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት መልካምንና ቅንን ነገር እውነትንም አደረገ። 21ስለ እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 31: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ