ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 30
30
ሕዝቅያስ ለፋሲካ በዓል ዝግጅት እንዳደረገ
1ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ፋሲካ ያደርጉ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፤ ደግሞም ወደ ኤፍሬምና ወደ ምናሴ ደብዳቤ ጻፈ። 2-3ካህናቱም በሚበቃ ቍጥር ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰባሰቡ፥ በጊዜው ያደርጉት ዘንድ አልቻሉምና ንጉሡና አለቆቹ የኢየሩሳሌምም ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ያደርጉ ዘንድ ተመካክረው ነበር። 4ነገሩም ለንጉሡና ለጉባኤው ሁሉ ዓይን መልካም ነበረ። 5እንደ ተጻፈም በብዙ ቍጥር አላደረጉም ነበርና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ያደርጉ ዘንድ እንዲመጡ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ ለእስራኤል ሁሉ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ። 6እንደ ንጉሡም ትእዛዝ መልክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የአለቆቹን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ፤ “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እግዚአብሔር ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጠ ቅሬታችሁ እንዲመለስ ወደ አብርሃምና ወደ ይስሐቅ ወደ እስራኤልም አምላክ ተመለሱ። 7እናንተም እንደምታዩ የተፈቱ እስኪያደርጋቸው ድረስ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። 8አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፤ ጽኑ ቍጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ። 9አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርምና፥ ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፤ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ።”
10መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ አገር እስከ ዛብሎን ሄዱ፤ እነዚያ ግን በንቀት ሳቁባቸው፤ አፌዙባቸውም። 11ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ ከዛብሎንም አያሌ ሰዎች ሰውነታቸውን አዋረዱ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። 12ደግሞም አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ቃል የሆነውን የንጉሡንና የአለቆቹን ትእዛዝ ያደርጉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ሆነ።
የፋሲካ በዓል መከበር
13በሁለተኛውም ወር የቂጣውን በዓል ያደርግ ዘንድ እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆነ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተከማቸ። 14ተነሥተውም በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ዕቃ ሁሉ አስወገዱ፤ በቄድሮንም ወንዝ ጣሉት። 15በሁለተኛውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም አፈሩ፤ ተቀደሱም፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ። 16እንደ እግዚአብሔርም ሰው እንደ ሙሴ ሕግ በሥርዓታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያን እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር። 17በጉባኤውም ያልተቀደሱ እጅግ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ይቀድሱአቸው ዘንድ ንጹሐን ላልሆኑት ሁሉ ፋሲካውን ያርዱላቸው ነበር። 18እንደ ትእዛዙም ሳይሆን ከኤፍሬምና ከምናሴ ከይሳኮርና ከዛብሎንም ወገን እጅግ ሰዎች ሳይነጹ ፋሲካውን በሉ። 19ሕዝቅያስም “ምንም እንደ መቅደሱ ማንጻት ባይነጻ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን የሚያቀናውን ሁሉ ቸሩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው” ብሎ ስለ እነርሱ ጸለየ። 20እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም ፈወሰ። 21በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አደረጉ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። 22ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ ያጽናና ነበር። የደኅንነትንም መሥዋዕት እያቀረቡ፥ የአባቶቻቸውንም አምላክ እያመሰገኑ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።
23-24የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ ስለ ቍርባን ሺህ ወይፈኖችና ሰባት ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥቶ ነበርና፥ አለቆቹም ሺህ ወይፈኖችና አሥር ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥተው ነበርና፥ ከካህናቱም እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና ጉባኤው ሁሉ እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል ያደርጉ ዘንድ ተማከሩ፤ በደስታም እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 25የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ከእስራኤልም የመጡ ጉባኤ ሁሉ፥ ከእስራኤልም አገር የመጡትና በይሁዳ የኖሩት እንግዶች ደስ አላቸው። 26በኢየሩሳሌምም ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር። 27ካህናቱና ሌዋውያኑም ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምጻቸውም ተሰማ፤ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱስ መኖሪያው ወደ ሰማይ ዐረገ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 30: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ