ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 29
29
ሕዝቅያስ በይሁዳ እንደነገሠ (2ገነ.18፥1-3)
1ሕዝቅያስም የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፤ በኢየሩሳሌም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ትባል ነበር። 2አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።
ሕዝቅያስ ቤተ መቅደሱን አነጻ
3በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያውም ወር የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ከፈተ፤ አደሳቸውም። 4ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፤ በምስራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፤ 5እንዲህም አላቸው፤ “ሌዋውያን ሆይ! ስሙኝ፤ ተቀደሱ፤ የአባቶቻችሁንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ቀድሱ፤ ርኩሱን ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ። 6አባቶቻችን ተላልፈዋል፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፤ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር መኖሪያ መልሰዋል፤ 7ወደ እርስዋም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ ደግሞም የወለሉን ደጆች ቈልፈዋል፤ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፤ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም። 8ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፤ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ፥ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው። 9እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ሚስቶቻችንም ተማረኩ። 10አሁንም የቍጣው ጽናት ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ። 11ልጆቼ ሆይ! በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።”
12ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፥ 13ከኤሊጸፋንም ልጆች ሺምሪና ይዒኤል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና መታንያ፥ 14ከኤማንም ልጆች ይሒኤልና ሰሜኢ፥ ከኤዶታምም ልጆች ሸማያና ዑዝኤል ተነሡ። 15ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው ተቀደሱ፤ በእግዚአብሔር ቃል እንደመጣው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ የእግዚአብሔርን ቤት ያነጹ ዘንድ ገቡ። 16ካህናቱም ያነጹት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጡ ገቡ፤ በእግዚአብሔርም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት። 17በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ይቀድሱ ጀመር፤ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ወለል ደረሱ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት በስምንት ቀን ቀደሱ፤ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ። 18ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው “የእግዚአብሔርን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ሕብስት ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤ 19ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፍ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ሆነዋል” አሉት።
የቤተ መቅደስ አምልኮ እንደገና መጀመር
20ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ የከተማይቱንም አለቆች ሰበሰበ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ወጣ። 21ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም ስለ ይሁዳም ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች ለኃጢያት መሥዋዕት አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን “በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አሳርጉአቸው” አላቸው። 22ወይፈኖቹንም አረዱ፤ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት። አውራ በጎቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት። 23የኃጢያትም መሥዋዕት የሚሆኑትን አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እጃቸውንም ጫኑባቸው፤ ካህናቱም አረዱአቸው፤ 24ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኃጢያት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተሰረያ ያደርጉ ዘንድ የኃጢያቱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።
25ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ቤት አቆመ። 26ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር። 27ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያ ላይ ያሳርጉ ዘንድ አዘዘ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ማረግ በተጀመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መዝሙር ደግሞ ተጀመረ፤ መለከቱም ተነፋ፤ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ ተመታ። 28ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፤ መዘምራኑም ዘመሩ፤ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ሆነ። 29ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ አጎነበሱ፤ ሰገዱም። 30ንጉሡም ሕዝቅያስና አለቆቹ ሌዋውያንን በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ አዘዙ። በደስታም አመሰገኑ፤ አጎነበሱ፤ ሰገዱም።
31ሕዝቅያስም “አሁን ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ቅረቡ፤ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ፤” ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ። 32ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ ወይፈን፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 33የተቀደሱትም ቍጥር ስድስት መቶ በሬዎች ሦስት ሺህም በጎች ነበረ። 34ነገር ግን ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ ጥቂቶች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር። 35የሚቃጠለውም መሥዋዕት የደኅንነቱም መሥዋዕት ስብ፥ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ሁሉ ጋር የሚቀርበው የመጠጥ ቍርባን፥ ብዙ ነበረ። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ። 36ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላዘጋጀላቸው ነገር ደስ አላቸው። ይህም ነገር በድንገት ተደረገ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 29: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ