ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 13

13
በአቢያና በኢዮርብዓም መካከል የተደረገ ጦርነት (1ነገ.15፥1-8)
1ንጉሡም ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። 2ሦስት ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ የእናቱም ስም ሚካያ ነበረ፤ የገብዓ ሰው የኡርኤል ልጅ ነበረች። 3በአብያና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ። አብያም የተመረጡትን አራት መቶ ሺህ ኃያላን ሰልፈኞችን ይዞ ወደ ሰልፍ ወጣ፤ ኢዮርብዓምም የተመረጡትን ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎችን ይዞ በእርሱ ላይ ተሰለፈ። 4አብያም በተራራማው በኤፍሬም አገር ባለው በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ“ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ሆይ! ስሙኝ፤ 5የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መንግሥትን ለዳዊትና ለልጆቹ በጨው ቃል ኪዳን ለዘላለም እንደ ሰጠ በውኑ አታውቁምን? 6የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን ተነሥቶ በጌታው ላይ ዐመፀ። 7ክፉዎች ሰዎችና ምናምንቴዎችም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሮብዓም ሕፃንና ለጋ በነበረበት ጊዜ፥ ሊቋቋማቸውም ባልቻለበት ጊዜ፥ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ላይ በረቱበት። 8አሁንም በዳዊት ልጆች እጅ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ ታስባላችሁ። እናንተም እጅግ ታላቅ ሕዝብ ናችሁ፤ ኢዮርብዓምም አማልክት አድርጎ የሠራላችሁ የወርቅ እምቦሶች ከእናንተ ጋር ናቸው። 9የአሮንን ልጆች፥ የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያን አላሳደዳችሁምን? እንደ ሌሎችም አሕዛብ ልማድ ካህናትን አላደረጋችሁምን? አንድ ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ይዞ ይቀድስ ዘንድ የሚመጣ ሁሉ አማልክት ላልሆኑት ለእነዚያ ካህን ይሆናል። 10ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ አልተውነውም፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች የአሮን ልጆች ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም በሥራቸው ከእኛ ጋር ናቸው። 11በየጥዋቱና በየማታውም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ጣፋጩን ዕጣን ያሳርጋሉ፤ የገጹንም ኅብስት በንጹሕ ገበታ ላይ፥ የወርቁን መቅረዝና ቀንዲሎቹን ማታ ማታ እንዲያበሩ ያዘጋጃሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንጠብቃለን፤ እናንተ ግን ትታችሁታል። 12እነሆም፥ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አለቃ ነው፤ መለከቱንም የሚነፉ ካህናቱ ከእኛ ጋር ናቸው፤ በእናንተም ላይ ይጮኸሉ። የእስራኤ ልጆች ሆይ፥ አይበጃችሁምና ከአባቶቻሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ።”
13ኢዮርብዓም ግን ድብቅ ጦር በስተኋላቸው አዞረ፤ እነርሱ በይሁዳ ፊት ሆነው ድብቅ ጦሩ በስተ ኋላቸው ነበረ። 14ይሁዳም ወደ ኋላው በተመለከተ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰልፉ በፊቱና በኋላው ነበረ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፤ ካህናቱም መለከቱን ነፉ። 15የይሁዳም ሰዎች ጮኹ፤ የይሁዳም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት መታቸው። 16የእስራኤልም ልጆች ከይሁዳ ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 17አብያና ሕዝቡ ታላቅ አመታት መቱአቸው፤ ከእስራኤልም አምስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎች ተገድለው ወደቁ። 18በዚያም ጊዜ የእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፤ የይሁዳም ልጆች በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነው ነበርና አሸነፉ። 19አብያም ኢዮርብዓምን አሳደደው፤ ከእርሱም ከተሞቹን ቤቴልንና መንደሮችዋን፥ ይሻናንና መንደሮችዋን፥ ዔፍሮንንና መንደሮችዋን ወሰደ። 20ኢዮርብዓምም ከዚያ በኋላ በአብያ ዘመን አልበረታም፤ እግዚአብሔርም ቀሰፈው፤ ሞተም። 21አብያም ጸና፤ ዐሥራ አራትም ሚስቶች አገባ፤ ሀያ ሁለትም ወንዶች ልጆችንና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆችን ወለደ። 22የአብያም የቀረው ነገርና አካሄዱ የተናገራቸውም ቃሎች በነቢዩ በአዶ መጽሐፍ ተጽፈዋል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ