ሳሙኤልም ሞተ፥ እስራኤልም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት። ዳዊትም ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ። በማዖንም የተቀመጠ አንድ ሰው ነበረ፥ ከብቱም በቀርሜሎስ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ሰው ነበረ፥ ለእርሱም ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፥ በቀርሜሎስም በጎቹን ይሸልት ነበር። የሰውዮውም ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበረ፥ የሴቲቱም አእምሮ ታላቅ፥ መልክዋም የተዋበ ነበረ፥ ሰውዮው ግን ባለጌ ነበረ፥ ግብሩም ክፉ ነበረ፥ ከካሌብም ወገን ነበረ። ዳዊትም በምድረ በዳ ሳለ፦ ናባል በጎቹን ይሸልታል የሚል ወሬ ሰማ። ዳዊትም አሥር ጕልማሶች ላከ ለጕልማሶችም አለ፦ ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ወደ ናባል ሂዱ፥ በስሜም ስለ ሰላም ጠይቁት፥ እንዲህም በሉት፦ በደኅንነት ኑር፥ ለአንተና ለቤትህም ለአንተም ላሉት ሁሉ ሰላም ይሁን። አሁንም በጎችህን እንድትሸልት ሰምቻለሁ፥ እረኞችህም ከእኛ ጋር ነበሩ፥ ከቶ አልበደልናቸውም፥ በቀርሜሎስም በተቀመጡበት ዘመን ሁሉ ከመንጋው አንዳች አልጎደለባቸውም። ጕልማሶችህን ጠይቃቸው፥ እነርሱም ይነግሩሃል፥ አሁንም እንግዲህ በመልካም ቀን መጥተንብሃልና ጕልማሶች በፊትህ ሞገስ ያግኙ፥ በእጅህም ከተገኘው ለባሪያዎችህና ለልጅህ ለዳዊት፥ እባክህ፥ ስጥ። የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነግረው ዝም አሉ። ናባልም ለዳዊት ባሪያዎች፦ ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኮበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው። እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን? ብሎ መለሰላቸው። የዳዊትም ጕልማሶች ዞረው በመጡበት መንገድ ተመለሱ፥ መጥተውም ይህን ነገር ሁሉ ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ሰዎቹን፦ ሁላችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ አላቸው። ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፥ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፥ አራት መቶ ሰዎችም ዳዊትን ተከትለው ወጡ፥ ሁለት መቶውም በዕቃው ዘንድ ተቀመጡ። ከብላቴኖቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ ብሎ ነገራት፦ እነሆ፥ ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ጌታችንን ሊባርኩ መልእክተኞች ላከ፥ እርሱ ግን ሰደባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን በእኛ ዘንድ እጅግ መልካም ነበሩ፥ አልበደሉንምም፥ ከእነርሱም በሄድንበት ዘመን ሁሉ በምድረ በዳ ሳለን አንዳች አልጠፋብንም፥ ከእነርሱ ጋር ሆነን መንጋውን በጠበቅንበት ዘመን ሁሉ ሌሊትና ቀን አጥር ሆነውን ነበር። ስለዚህም በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ክፉ ነገር እንዲመጣ ተቆርጦአልና፥ እርሱ ምናምንቴ ሰው ስለ ሆነ ማንም ሊናገረው አይችልምና የምታደርጊውን ተመልከቺና እወቂ። አቢግያም ፈጥና ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስትም የተዘጋጁ በጎች፥ አምስትም መስፈሪያ ጥብስ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ዘቢብ፥ ሁለት መቶም የበለስ ጥፍጥፍ ወሰደች፥ በአህዮችም ላይ አስጫነች። ለብላቴኖችዋም፦ አስቀድማችሁ በፊቴ ሂዱ፥ እነሆም፥ እከተላችኋለሁ አለች። ይህንም ለባልዋ ለናባል አልነገረችውም። እርስዋም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ በተራራው ላይ በተሰወረ ስፍራ በወረደች ጊዜ፥ እነሆ፥ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርስዋ ወረዱ፥ እርስዋም ተገናኘቻቸው። ዳዊትም፦ ለዚህ ሰው ከሆነው ሁሉ አንድ ነገር እንዳይጠፋበት በእውነት ከብቱን ሁሉ በምድረ በዳ በከንቱ ጠበቅሁ፥ እርሱም ስለ በጎነቴ ክፋት መለሰልኝ። ለእርሱም ከሆነው ሁሉ እስከ ነገ ጥዋት ድረስ አንድ ወንድ ስንኳ ብተው እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያድርግ እንዲህም ይጨምር ብሎ ነበር።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos