ሳሙኤል ሞተ፤ መላው እስራኤላውያንም በአንድነት መጥተው አለቀሱለት፤ ከዚያም በኋላ በራማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ቀበሩት። ከዚያም በኋላ ዳዊት ወደ ፋራን ምድረ በዳ ሄደ፤ በዚያም ቤተሰቡ ከካሌብ ጐሣ የሆነ ናባል ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የማዖን ተወላጅ ሲሆን በቀርሜሎስ ከተማ አጠገብ የእርሻ መሬት ነበረው፤ ታላቅ ባለጸጋ ከመሆኑም የተነሣ ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፤ ሚስቱ አቢጌልም እጅግ የተዋበች አስተዋይ ሴት ስትሆን እርሱ ግን መልካም ጠባይ የጐደለው ባለጌ ሰው ነበር። ናባል በቀርሜሎስ በጎቹን ያሸልት ነበር፤ ዳዊትም በበረሓ ሳለ ይህንኑ ወሬ ሰማ፤ ስለዚህም ዐሥር መልእክተኞችን መርጦ ወደ ቀርሜሎስ እንዲሄዱና ናባልን አግኝተው የእርሱን ሰላምታ እንዲያቀርቡለት አዘዛቸው፤ ለናባልም ይነግሩት ዘንድ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፦ “ሰላም ላንተ፥ ሰላም ለቤትህ፥ ሰላም ያንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን ብላችሁ ሰላምታ አቅርቡለት። በጎችህንም እንደምታሸልት ሰምቶአል፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜም ሁሉ ምንም ዐይነት ጒዳት እንዳላደረስንባቸው እንድታውቅ ይፈልጋል፤ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ከመንጋቸው አንድ እንኳ አልተወሰደባቸውም፤ እነርሱንም ብትጠይቃቸው ይህንኑ ይነግሩሃል፤ እነሆ ዛሬ እኛ የደስታ ግብዣ በሚደረግበት ቀን መጥተናል፤ እኛንም በመልካም ሁኔታ ትቀበለን ዘንድ ዳዊት ጠይቆአል፤ ስለዚህ ለእኛ ለአገልጋዮችህና ለወዳጅህ ለዳዊት ስትል የሚቻልህን ስጦታ አድርግልን።” የዳዊት ሰዎችም ይህንኑ መልእክት በዳዊት ስም ለናባል አስረክበው ይጠባበቁ ጀመር፤ ናባልም በመጨረሻ “ኧረ ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው? እኔ ስለ እርሱ ሰምቼም አላውቅም! እነሆ፥ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከጌቶቻቸው በኰበለሉ አገልጋዮች ተሞልታለች! ስለዚህ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም ለበጎች ሸላቾቼ ያረድኳቸውን እንስሶች አንሥቼ ከወዴት እንደ መጡ ለማላውቃቸው ሰዎች የምሰጥበት ምክንያት የለም!” አለ። መልእክተኞቹም ተመልሰው መጥተው ናባል ያለውን ሁሉ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም “በሉ ሰይፋችሁን ታጠቁ!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ ዳዊትም ራሱ ሰይፉን ታጠቀ፤ ጓዝ የሚጠብቁ ሁለት መቶ ሰዎች ወደ ኋላ ትቶ አራት መቶ ሰዎች በማስከተል ገሥግሦ ለመሄድ ተነሣ። ከናባል አገልጋዮች አንዱም የናባልን ሚስት አቢጌልን እንዲህ አላት፤ “ዳዊት ካለበት በረሓ መልእክተኞችን ከሰላምታ ጋር ወደ ጌታችን ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን በስድብ አዋረዳቸው፤ እነርሱ ግን ለእኛ በጎ አድራጊዎች ነበሩ፤ ምንም ችግር አልፈጠሩብንም፤ ከእነርሱ ጋር በዱር በነበርንበት ጊዜ ሁሉ ከእንስሶቻችን አንድ እንኳ ተሰርቆብን አያውቅም፤ መንጋዎቻችንን እየጠበቅን በቈየንበት ጊዜ ሁሉ በቀንም ሆነ በሌሊት እነርሱ ለእኛ አጥር ሆነውን ነበር። እባክሽን ይህን ጉዳይ አስቢበትና ማድረግ ስለሚገባሽ ነገር ወስኚ፤ አለበለዚያ ለጌታችንና ለቤተሰቡ ሁሉ አደገኛ ጥፋት ይሆናል፤ እርሱ እንደ ሆነ የማንንም ምክር የማይሰማ ደረቅ ሰው ነው!” አቢጌልም በፍጥነት ሁለት መቶ እንጀራ፥ ወይን ጠጅ የተሞላበት ሁለት የወይን አቁማዳ፥ አምስት የተጠበሱ በጎች፥ ዐሥራ ሰባት ኪሎ የተጠበሰ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ወይንና ሁለት መቶ የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ በአንድነት ሰብስባ በአህዮች ላይ ጫነች። ከዚህም በኋላ አገልጋዮቹን “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋላሁ” አለቻቸው፤ ለባልዋ ግን የነገረችው ቃል አልነበረም። እርስዋም በአህያ ላይ ተቀምጣ እየጋለበች በኮረብታው ጥግ በሚገኘው ጠመዝማዛ መንገድ ስትወርድ በድንገት ዳዊትና ተከታዮቹ ወደ እርስዋ ሲመጡ አገኘቻቸው፤ ዳዊትም በልቡ እንዲህ እያለ ያስብ ነበር፤ “የዚያን የማይረባ ሰው ሀብት በዚህ በረሓ ለምን ስጠብቅ ቈየሁ? የእርሱ ከሆነው ንብረት ምንም ነገር ተሰርቆበት አያውቅም፤ ታዲያ እኔ ስላደረግሁለት መልካም ነገር እርሱ የሚከፍለኝ ወሮታ ይህ ሆኖ ቀረ! ከመንጋቱ በፊት የእርሱ የሆኑትን ወንዶች ሁሉ አንድ እንኳ ሳላስቀር በሙሉ ሳልገድል ብቀር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!”
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos