አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:12-36

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:12-36 አማ54

የዔሊም ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፥ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር። የካህናትም ልማድ በሕዝቡ ዘንድ እንዲህ ነበረ፥ ሰው ሁሉ መሥዋዕት ሲያቀርብ ሥጋው በተቀቀለ ጊዜ የካህኑ ሎሌ ይመጣ ነበረ፥ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበረ፥ ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰድድው ነበር፥ ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር። ወደዚያም በመጡት በእስራኤላውያን ላይ በሴሎ እንዲህ ያደርጉ ነበር። ደግሞም ስቡን ሳያቃጥሉ የካህኑ ሎሌ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፦ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ ይለው ነበር። ሰውዮውም፦ አስቀድሞ ስቡን ያቃጥሉት ኋላም ሰውነትህ ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ ቢለው፥ እርሱ፦ አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፥ እንቢም ብትል በግድ እወስደዋለሁ ይለው ነበር። ሰዎቹም የእግዚአብሔርን ቁርባን ይንቁ ነበርና የጎበዛዝቱ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች። ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፋድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፥ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን፦ ለእግዚአብሔር ስለ ተሳለችው ስጦታ ፋንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ ብሎ ባረካቸው፥ እነርሱም ወደ ቤታቸው ሄዱ። እግዚአብሔርም ሐናን አሰበ፥ ፀነሰችም፥ ሦስት ወንዶችና ሁለትም ሴቶች ልጆች ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ። ዔሊም እጅግ አረጀ፥ ልጆቹም በእስራኤል ሁሉ ላይ ያደረጉትን ሁሉ፥ በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደ ተኙ ሰማ። እርሱም አላቸው፦ ስለ ክፉ ሥራችሁ ከዚህ ሕዝብ ሁሉ ሰምቻለሁና ስለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? ልጆቼ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአተኛ በማድረጋችሁ ስለ እናንተ የደረሰኝ ወሬ መልካም አይደለምና ይህ አይሆንም። ሰውስ ሰውን ቢበድል እግዚአብሔር ይፈርድበታል ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ የሚለምን ማን ነው? እነርሱ ግን እግዚአብሔር ሊገድላቸው ወድዶአልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም። ብላቴናውም ሳሙኤል እያደገ ሄደ፥ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ። የእግዚአብሔርም ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ አለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ በግብጽ በፈርዖን ቤት ባሪያ ሳለ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፥ ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬ ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ ኤፋድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ ለእኔ መረጥሁት፥ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። በማደሪያዬ ያቀርቡት ዘንድ ያዘዝሁትን መሥዋዕቴንና ቍርባኔን ስለ ምን ረገጣችሁ? እንድትወፍሩም የሕዝቤን የእስራኤልን ቍርባን ሁሉ መጀመሪያ በመብላታችሁ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርህ? ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእውነት ቤትህ የአባትህም ቤት ለዘላለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፥ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም። እነሆ፥ ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ፥ ክንድህን የአባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል። በእስራኤል በረከት ሁሉ፥ በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ በቤትህም ለዘላለም ሽማግሌ አይገኝም። ከመሠዊያዬ ያልተቆረጠ ልጅህ ቢገኝ ዓይንህን ያፈዝዘዋል፥ ነፍስህንም ያሳዝናል ከቤትህም የሚወለዱ ሰዎች ሁሉ በጎልማስነት ይሞታሉ። ይህ በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፥ ሁለቱ በአንድ ቀን ይሞታሉ። የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፥ በልቤም በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፥ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል። ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፥ በፊቱም ሰግዶ፦ ቁራሽ እንጀራ እበላ ዘንድ ከካህናት ወደ አንዲቱ ዕጣ፥ እባክህ፥ ስደደኝ ብሎ አንድ ብር አንድ እንጀራም ይለምናል።