የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:12-36

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2:12-36 አማ05

የዔሊ ልጆች ምንም የማይረቡ ስድ አደጎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያከብሩም ነበር፤ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደዚህ ነበር፦ ሰው ሁሉ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ሥጋው በመብሰል ላይ እያለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይቀርብ ነበር። እርሱም ሜንጦውን ወደ ድስቱ፥ ወይም ወደ ምንቸቱ፥ ወይም ወደ አፍላሉ፥ ወይም ወደ ቶፋው ይከተው ነበር፤ ሜንጦው የሚያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለራሱ ይወስደው ነበር፤ ይህንንም ድርጊት ወደ ሴሎ በሚመጡት እስራኤላውያን ሁሉ ላይ ያደርጉት ነበር። ከዚህም በቀር ጮማው ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መሥዋዕቱን ወደሚሠዋው ሰው መጥቶ “ካህኑ ያንተን የተቀቀለ ሥጋ ሳይሆን ጥሬ ሥጋ ስለሚፈልግ ለእርሱ እንድጠብስለት ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። ሰውየውም “በመጀመሪያ ስቡን ያቃጥሉትና ከዚያ በኋላ የፈለግኸውን ትወስዳለህ” ቢለው፥ የካህኑ አገልጋይ “አይሆንም! አሁኑኑ ስጠኝ! እምቢ ብትል ግን በግድ እወስዳለሁ!” ይለው ነበር። በዚህም ዐይነት የእግዚአብሔርን መሥዋዕት ስላቃለሉ የዔሊ ልጆች ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ከፍተኛ ነበር። ሳሙኤል ግን ገና በልጅነቱ ከበፍታ የተሠራ ሸሚዝ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር፤ ይህም ቃል በዕብራይስጡ ካህኑ ለሚለብሰው ልብስ ወይም በደረቱ ላይ ስለሚያደርገው ነገር መጠሪያ ነው። እናቱም በየዓመቱ ባልዋን ተከትላ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለማቅረብ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ዔሊም ሕልቃናን ከሚስቱ ከሐና ጋር በሚመርቅበት ጊዜ፥ ሕልቃናን “ለእግዚአብሔር የተለየ አድርጋችሁ በሰጣችሁት በዚህ ልጅ ፈንታ ከዚህቹ ሴት ሌሎችን ልጆች ይስጥህ!” ይለው ነበር። ከዚያን በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። እግዚአብሔርም ሐናን አስታወሳትና ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች፤ ወጣቱ ሳሙኤልም እግዚአብሔርን እያገለገለ አደገ። እነሆ ዔሊ በዕድሜው አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በእስራኤላውያን ላይ የሚያደርጉት ክፉ ነገርና በድንኳኑ ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር እንደሚያመነዝሩ ሰማ። ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ይህን ክፉ ነገር ታደርጋላችሁ? የምታደርጉትን ክፉ ነገር ሁሉ ከእያንዳንዱ ሰው ሰምቼዋለሁ፤ ልጆቼ ሆይ! በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ስለ እናንተ የተሠራጨው ወሬ መልካም አይደለምና እንዲህ ያለ ክፉ ነገር አታድርጉ! አንድ ሰው ሌላውን ሰው ቢበድል፥ እግዚአብሔር በመታደግ ሊያድነው ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚበድል ሰው ማን ሊያማልደው ይችላል?” ሆኖም እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ቊርጥ ውሳኔ ስላደረገ የዔሊ ልጆች የአባታቸውን ምክር አልሰሙም። ወጣቱ ሳሙኤል ግን በቁመት እያደገ፥ በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ ጸጋና ሞገስን እያገኘ ሄደ። ከእግዚአብሔር የተላከ አንድ ነቢይ ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በፈርዖን ቤት ባሪያዎች በነበሩ ጊዜ ለቀድሞ አባትህ ለአሮን ራሴን ገለጥሁለት፤ እርሱንም ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፥ እጣን እንዲያጥን፥ በፊቴ ኤፉድ እንዲለብስ፥ የእኔ ካህን ይሆን ዘንድ መረጥሁት፤ ለቀድሞ አባትህ ልጆችም የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡትን የሚቃጠል መሥዋዕት ሰጠኋቸው። በትእዛዜ መሠረት የሚቀርብልኝን መሥዋዕትና ቊርባን ለምን ታዋርዳላችሁ? ልጆችህ ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ምርጥ የሆነውን እየወሰዱ በመብላት ይወፍሩ ዘንድ እነርሱን ከእኔ ይበልጥ የምታከብራቸው ለምንድነው?’ ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የአንተ ቤተሰብና የቀድሞ አባትህ ቤተሰብ ለዘለዓለም ያገለግሉኝ ዘንድ ቃል ገብቼ ነበር፤ አሁን ግን እንዲህ አይሆንም፤ የሚያከብሩኝን አከብራለሁ የሚንቁኝም ይናቃሉ። እነሆ፥ ከአንተ ቤተሰብ መካከል አንድም ሰው ወደ ሽምግልና ዕድሜ እንዳይደርስ አንተንና የአባቶችህን ቤተሰብ የማጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ ነው። እነሆ እኔ በምመለክበት ቦታ ብዙ ችግር ታያለህ፤ በእስራኤል ዘንድ በጎ ነገር የሚደረግ ቢሆንም ከአንተ ቤተሰብ መካከል ማንም ረጅም ዕድሜ የሚኖረው አይገኝም። በመሠዊያዬ ከምታገለግሉት ከእናንተ መካከል ሳላጠፋ የማስቀረው አንድ ሰው ዐይንህን በእንባ የሚያጠፋና ልብህን የሚያሳዝን ይሆናል፤ የቤተሰብህ አባሎች ሁሉ ግን በወጣትነት ዕድሜአቸው በሰይፍ ያልቃሉ፤ የሁለቱ ልጆችህ የሖፍኒና የፊንሐስ ዕድል ፈንታ ምልክት ይሆንሃል፤ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ። ለእኔም እንደ ልቤና እንደ ሐሳቤ የሚያደርግ አንድ ታማኝ ካህን አስነሣለሁ፤ ለእርሱም የጸና ዘር እመሠርትለታለሁ፤ እኔ በቀባሁትም ንጉሥ ፊት ይመላለሳል። ከአንተ ዘሮች መካከል በሕይወት የሚተርፍ ሁሉ ወደዚያ ካህን ዘንድ እየሄደ ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት ከእርሱ ገንዘብና ምግብ ይለምናል፤ የዕለት ምግብ ብቻ ለማግኘትም ሲል ካህናትን በረዳትነት ማገልገል እንዲፈቀድለት ይለምናል።’ ”