አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:41-47

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:41-47 አማ54

ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፥ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፥ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፥ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፥ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፥ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፥ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።