1 ሳሙኤል 17:41-47
1 ሳሙኤል 17:41-47 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና፥ መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትርና ድንጋይ ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው። ዳዊትም፥ “የለም ከውሻ ትከፋለህ” አለው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን በአምላኮቹ ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “ወደ እኔ ና፤ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣቸዋለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊዉን አለው፥ “አንተ ሰይፍና ጦር፥ ጋሻም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፤ ራስህንም ከአንተ እቈርጠዋለሁ፤ ሬሳህንና የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ምድር ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንዳለ ያውቃሉ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቃል። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እግዚአብሔርም እናንተን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።”
1 ሳሙኤል 17:41-47 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም፣ “እስኪ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት ጌታ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቈርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፣ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።”
1 ሳሙኤል 17:41-47 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፥ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፥ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፥ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፥ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፥ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፥ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።
1 ሳሙኤል 17:41-47 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ወደ ዳዊት ለመቅረብ መራመድ ጀመረ፤ ጋሻጃግሬውም በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር፤ ዳዊት ቀይ፥ መልከ መልካም፥ ትንሽ ልጅ ስለ ነበረ ዳዊትን ጎልያድ ትኲር ብሎ ባየው ጊዜ በንቀት ዐይን ተመለከተው፤ ስለዚህም ጎልያድ ዳዊትን “በትር ይዘህ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝን” ካለው በኋላ በአማልክቱ ስም ረገመው። ቀጥሎም “ወዲህ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞራዎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ሾተል ይዘህ መጥተህብኛል፤ እኔ ደግሞ አንተ በምትፈታተነውና በእስራኤል ሠራዊት አምላክ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፤ በዚህች ቀን እግዚአብሔር በአንተ ላይ ድልን ያጐናጽፈኛል፤ እኔም ራስህን እቈርጣለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ወታደሮች ሥጋ ለአሞራዎችና ለአራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ መላው ዓለም በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡት ሁሉ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍና በጦር አለመሆኑን ያውቃሉ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነውና፤ በእናንተም ላይ ድልን እንድንጐናጸፍ ያደርገናል።”
1 ሳሙኤል 17:41-47 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፍልስጥኤማዊውም፥ ጋሻ ጃግሬውን ከፊት ከፊቱ በማስቀደም፥ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። እርሱም ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው፥ ደም ግባት ያለው፥ መልከ መልካምና ልጅ ነበር፤ ስለዚህ በንቀት ዐይን ተመለከተው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። እርሱም ዳዊትን፥ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፥ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሠራዊት አምላክ በሆነው፥ ሁሉን በሚችል በሠራዊት ጌታ ስም እመጣብሃለሁ። ጌታ ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቆርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፤ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ እግዚአብሔር መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ ጌታ ያለ ሰይፍ ወይም ያለ ጦር እንደሚያድን ያውቃሉ፤ ሰልፉ የጌታ ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።”