አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:41-47

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17:41-47 አማ05

ፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ወደ ዳዊት ለመቅረብ መራመድ ጀመረ፤ ጋሻጃግሬውም በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር፤ ዳዊት ቀይ፥ መልከ መልካም፥ ትንሽ ልጅ ስለ ነበረ ዳዊትን ጎልያድ ትኲር ብሎ ባየው ጊዜ በንቀት ዐይን ተመለከተው፤ ስለዚህም ጎልያድ ዳዊትን “በትር ይዘህ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝን” ካለው በኋላ በአማልክቱ ስም ረገመው። ቀጥሎም “ወዲህ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞራዎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ሾተል ይዘህ መጥተህብኛል፤ እኔ ደግሞ አንተ በምትፈታተነውና በእስራኤል ሠራዊት አምላክ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፤ በዚህች ቀን እግዚአብሔር በአንተ ላይ ድልን ያጐናጽፈኛል፤ እኔም ራስህን እቈርጣለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ወታደሮች ሥጋ ለአሞራዎችና ለአራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ መላው ዓለም በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡት ሁሉ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍና በጦር አለመሆኑን ያውቃሉ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነውና፤ በእናንተም ላይ ድልን እንድንጐናጸፍ ያደርገናል።”