አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:11-18

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:11-18 አማ54

እርሱም “ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም፤” አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዐለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጎናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ “ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። እርሱም “ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ፤” አለ። እግዚአብሔርም አለው “ሂድ፤ በመጣህበትም መንገድ በምድረ በዳ ወደ ደማስቆ ተመለስ፤ ከዚያም በደረስህ ጊዜ በሶርያ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ አዛሄልን ቅባው፤ በእስራኤልም ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ የናሜሲን ልጅ ኢዩን ቅባው፤ በፋንታህም ነቢይ ይሆን ዘንድ የአቤልምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው። ከአዛሄልም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ፥ ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩም ሰይፍ ያመለጠውን ሁሉ ኤልሳዕ ይገድለዋል። እኔም ከእስራኤል ጕልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ።”