አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:11-18

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:11-18 አማ05

እግዚአብሔርም ኤልያስን “ካለህበት ወጥተህ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም” አለው፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በአጠገቡ አለፈ፤ ብርቱ ነፋስም በፊቱ በመላክ ኰረቶችን ሰነጣጠቀ፤ አለቶችንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ነፋሱም ከቆመ በኋላ ምድሪቱ ተናወጠች፤ እግዚአብሔር ግን በምድሪቱ ነውጥ ውስጥ አልነበረም፤ ከምድሪቱም ነውጥ በኋላ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳት ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም በኋላ የሹክሹክታ ድምፅ ተሰማ። ኤልያስ የሹክሹክታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጐናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው መግቢያ በር አጠገብ ቆመ፤ አንድ ድምፅም “ኤልያስ ሆይ! እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኤልያስም “ሁሉን የምትችል አምላኬ ሆይ! እኔ ለአምላክነትህ በመቅናት ዘወትር አንተን ብቻ አገለግላለሁ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን ከአንተ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ መሠዊያዎችህንም ሰባብረዋል፤ ነቢያትንም ሁሉ ገድለዋል፤ እነሆ እኔ ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን እኔን እንኳ ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በደማስቆ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓ ተመልሰህ ሂድ፤ እዚያም በደረስህ ጊዜ አዛሄልን ቀብተህ በሶርያ ላይ አንግሠው፤ የኒምሺን ልጅ ኢዩንም ቀብተህ በእስራኤል ላይ አንግሠው፤ የአቤል መሖላ ተወላጅ የሆነውን የዮሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕንም ቀብተህ በአንተ እግር ነቢይ እንዲሆን አድርገው። ከአዛሄል እጅ ከመገደል ተርፎ የሚያመልጠውን ማንኛውንም ሰው ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ እጅ የሚያመልጠውንም ኤልሳዕ ይገድለዋል። ይሁን እንጂ ለእኔ ታማኞች የሆኑ፥ ለባዓል ያልሰገዱና ምስሉንም ያልተሳለሙ ሰባት ሺህ ሰዎችን በእስራኤል ምድር በሕይወት እንዲተርፉ አደርጋለሁ።”