የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 13:1-10

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 13:1-10 አማ54

ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፥ እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ በመሠዊያውም ላይ “መሠዊያ ሆይ! መሠዊያ ሆይ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፤ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል፤” ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ። በዚያም ቀን “እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው፤ እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል፤” ብሎ ምልክት ሰጠ። ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ “ያዙት!” አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፤ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ። ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው “አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፤ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ፤” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞም ሆነች። ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፤ እንጀራም ብላ፤ በረከትም እሰጥሃለሁ፤” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን “የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፤ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤ ‘እንጀራ አትብላ፤ ውሃም አትጠጣ፤ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ፤’ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና፤” አለው። በሌላም መንገድ ሄደ፤ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም።