አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11
11
ዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ እንደ ሆነ
(2ሳሙ. 5፥1-5)
1እስራኤልም ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት ተሰብስበው “እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቍራጭ ነን፤ 2አስቀድሞ ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም ‘ሕዝቤን እስራኤልን አንተ ትጠብቃለህ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆናለህ፤’ ብሎህ ነበር፤” አሉት። 3የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደረገ፤ በሳሙኤልም እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት።
ዳዊት ኢየሩሳሌምን እንደ ያዘ
(2ሳሙ. 5፥6-10)
4ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባል ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፤ በአገሩም የተቀመጡ ኢያቡሳውያን በዚያ ነበሩ። 5በኢያቡስም የተቀመጡ ዳዊትን “ወደዚህ አትገባም፤” አሉት፤ ዳዊት ግን አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፤ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት። 6ዳዊትም “ኢያቡሳውያንን አስቀድሞ የሚመታ ሰው አለቃና መኮንን ይሆናል፤” አለ። የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ አስቀድሞ ወጣ፤ አለቃም ሆነ። 7ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፤ ስለዚህም “የዳዊት ከተማ” ብለው ጠሩአት።
8ከሚሎም ጀምሮ በዙሪያው ከተማ ሠራ፤ ኢዮአብም የቀረውን ከተማ አበጀ። 9ዳዊትም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና እየበረታ ሄደ።
የዳዊት ኀያላን የጦር አለቆች
(2ሳሙ. 23፥8-39)
10ለዳዊትም የነበሩት የኃያላን አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ስለ እስራኤል እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያነግሡት ዘንድ ከእስራኤል ሁሉ ጋር በመንግሥቱ ላይ አጸኑት። 11የዳዊትም ኀያላን ቍጥር ይህ ነበረ፤ የሠላሳው አለቃ የሐክሞናዊው ልጅ ያሾብዓም ነበረ፤ እርሱ ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ ገደለ። 12ከእርሱም በኋላ በሦስቱ ኀያላን መካከል የነበረ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነበረ። 13እርሱ ከዳዊት ጋር በፈስደሚም ነበረ፤ በዚያም ገብስ በሞላበት እርሻ ውስጥ ፍልስጥኤማውያን ለሰልፍ ተሰብስበው ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 14በእርሻውም መካከል ቆመው ጠበቁት፤ ፍልስጥኤማውያንንም ገደሉ፤ እግዚአብሔርም በታላቅ ማዳን አዳናቸው።
15ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓለቱ ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 16በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በቤተ ልሔም ነበረ። 17ዳዊትም “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ምንጭ ውሃ ማን ይሰጠኛል?” ብሎ ተመኘ። 18እነዚህም ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ቀድደው ሄዱ፤ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፍስሶ 19“ይህን አደርግ ዘንድ አምላኬ ይከልክለኝ፤ በነፍሳቸው የደፈሩትን የእነዚህን ሰዎች ደም እጠጣለሁን? በነፍሳቸው አምጥተውታል፤” አለ። ስለዚህም ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱም ኀያላን ያደረጉት ይህ ነው።
20የኢዮአብም ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ፤ ጦሩንም በሦስት መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፤ በሦስቱም መካከል ስሙ የተጠራ ነበረ። 21በሁለተኛውም ተራ በሆኑት በሦስቱ መካከል የከበረ ነበረ፤ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም 22በቀብስኤልም የነበረው፥ ታላቅ ሥራ ያደረገው የጽኑዕ ሰው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊን የአሪኤልን ሁለቱን ልጆች ገደለ፤ በአመዳይም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። 23ቁመቱም አምስት ክንድ የነበረውን ረጅሙን ግብጻዊውን ሰው ገደለ፤ በግብጻዊውም እጅ የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር ነበረ፤ እርሱ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፤ ከግብጻዊው እጅ ጦሩን ነቅሎ በገዛ ጦሩ ገደለው። 24የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኃያላን መካከል የተጠራ ነበረ። 25እነሆ፥ ከሠላሳው ይልቅ የከበረ ነበረ፤ ነገር ግን ወደ ፊተኞቹ ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም በዘበኞቹ ላይ ሾመው።
26ደግሞም በጭፍሮች ዘንድ የነበሩት ኀያላን እነዚህ ናቸው፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ 27ሃሮራዊው ሳሞት፥ ፈሎናዊው ሴሌስ፥ 28የቴቁሔ ሰው የዒስካ ልጅ ዒራስ፥ ዓናቶታዊው አቢዔዜር፥ 29ኩሳታዊው ሴቤካይ፥ አሆሃዊው ዔላይ፥ 30ነጦፋዊው ኖኤሬ፥ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፥ 31ከብንያም ወገን ከጊብዓ የሪባይ ልጅ ኤታይ፥ ጲርዓቶናዊው በናያስ፥ 32የገዓስ ወንዝ ሰው ኡሪ፥ ዓረባዊው አቢኤል፥ 33ባሕሩማዊው ዓዝሞት፥ ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ 34የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፥ የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፥ 35የአሮዳዊው የአራር ልጅ አምናን፥ የኡር ልጅ ኤሊፋል፥ 36ምኬራታዊው ኦፌር፥ ፍሎናዊው አኪያ፥ 37ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፥ የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፥ 38የናታንም ወንድም ኢዮኤል፥ የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፥ 39አሞናዊው ጼሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፥ 40ይትራዊው ዒራስ፥ ይትራዊው ጋሬብ፥ 41ኬጢያዊው ኦርዮ፥ የአሕላይ ልጅ ዛባድ፥ 42የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፥ እርሱ የሮቤላውያን አለቃ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሰዎች ነበሩ፤ 43የማዕካ ልጅ ሐናን፥ ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፥ 44አስታሮታዊው ዖዝያ፥ የአሮዔራዊው የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፥ 45የሺምሪ ልጅ ይዲኤል፥ ወንድሙም ቲዳዊው ዮሐ፥ 46መሐዋዊው ኤሊኤል፥ ይሪባይ፥ ዮሻውያ፥ የኤልነዓም ልጆች፥ ሞዓባዊው ይትማ፥ 47ኤሊኤል፥ ዖቤድ፥ ምጾባዊው የዕሢኤል።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 11: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ