አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10
10
ንጉሥ ሳኦልና ልጆቹ እንደ ሞቱ
(1ሳሙ. 31፥1-13፤ 2ሳሙ. 1፥4-12)
1ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ። 2ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። 3ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፤ ቀስተኞችም አገኙት፤ ከቀስተኞቹም የተነሣ ተጨነቀ። 4ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን “እነዚህ ቈፋን መጥተው እንዳይዘብቱብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ፤” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና “እንቢ” አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ። 5ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 6ሳኦልና ሦስቱም ልጆቹ የቤቱም ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።
7በሸለቆውም የነበሩት የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው። 8በነጋውም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልንና ልጆቹን በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። 9ገፈፉትም፤ ራሱንና መሣሪያውንም አንሥተው ለጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምስራች ይወስዱ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ዙሪያ ሰደዱ። 10መሣሪያውንም በአምላኮቻቸው ቤት ውስጥ አኖሩ፤ ራሱንም በዳጎን ቤት ውስጥ ቸነከሩት። 11የኢያቢስ ገለዓድም ሰዎች ሁሉ ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ 12ጽኑዓን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፤ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከትልቁ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፤ ሰባት ቀንም ጾሙ። 13እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኀጢአት፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። 14ደግሞም መናፍስት ጠሪ ስለ ጠየቀ፥ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 10: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ