እኔ ተኝቼ ነበር፥ ልቤ ግን ነቅታ ነበር፤ ልጅ ወንድሜ ቃል ደጅ እየመታ መጣ፥ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ መደምደሚያዬ ሆይ፥ በራሴ ጠል፥ በቍንዳላዬም የሌሊት ነጠብጣብ ሞልቶበታልና ክፈችልኝ። ቀሚሴን አወለቅሁ፥ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፥ እንዴት አሳድፈዋለሁ? ልጅ ወንድሜ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከች። ለልጅ ወንድሜ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፤ እጆች በደጁ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥ ጣቶች ፈሳሹን ከርቤ አንጠባጠቡ። ለልጅ ወንድሜ ከፈትሁለት፥ ልጅ ወንድሜ ግን ሂዶ ነበር። ነፍሴ ከቃሉ የተነሣ ደነገጠች፤ ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፤ ጠራሁት፥ አልመለሰልኝም። ከተማዪቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፤ ቅጥር ጠባቂዎችም የዐይነ ርግብ መሸፈኛዬን ከራሴ ላይ ወሰዱት። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ በምድረ በዳ ኀይልና ጽንዐት አምላችኋለሁ፤ ልጅ ወንድሜን ያገኛችሁት እንደ ሆነ፥ እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ትነግሩት ዘንድ። አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከወንድሞች ልጆች ይልቅ ልጅ ወንድምሽ ማን ነው? ይህን ያህል መሐላ አምለሽናልና ከወንድሞች ልጆች ይልቅ ልጅ ወንድምሽ ማን ነው? ወንድሜ ነጭና ቀይ ነው፥ ከአእላፍ የተመረጠ ነው። ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፤ ቈንዳላው የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቍራ ጥቍረትም ጥቁር ነው። ዐይኖቹ በሙሉ የውኃ ኵሬ አጠገብ እንዳሉ በወተት እንደ ታጠቡ በኵሬ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ፥ እንደ ርግቦች ናቸው። ጕንጮቹ ሽቱን የሚያፈስሱ የሽቱ መደብ ናቸው። ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥ የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠባጥባሉ። እጆቹ የተርሴስ ፈርጥ እንዳለባቸው እንደ ለዘቡ የወርቅ ቀለበቶች ናቸው፤ ሆዱ በሰንፔር ዕንቍ እንዳጌጠ እንደ ዝሆን ጥርስ ነው፥ እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ እንደ ተመሠረቱ እንደ ዕብነ በረድ ምሰሶዎች ናቸው፤ መልኩ እንደ ሊባኖስና እንደ ዝግባ ዛፍ የተመረጠ ነው። ጕሮሮው እጅግ ጣፋጭ ነው፥ ሁለንተናውም የተወደደ ነው፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ልጅ ወንድሜ ይህ ነው፥ ወዳጄም ይህ ነው።
መሓልየ መሓልይ ዘሰሎሞን 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መሓልየ መሓልይ ዘሰሎሞን 5:2-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች