ማሕልየ መሓልይ 5:2-16

ማሕልየ መሓልይ 5:2-16 NASV

እኔ ተኝቻለሁ፤ ልቤ ግን ነቅቷል፤ ስሙ! ውዴ በር ያንኳኳል፤ እንዲህ ይላል፤ “እኅቴ ወዳጄ፣ ርግቤ፣ አንቺ እንከን የሌለብሽ፤ ክፈቺልኝ። ራሴ በጤዛ፣ ጠጕሬም በሌሊቱ ርጥበት ረስርሷል።” ቀሚሴን አውልቄአለሁ፤ ታዲያ እንዴት እንደ ገና ልልበስ? እግሬን ታጥቤአለሁ፤ እንዴት እንደ ገና ላቈሽሸው? ውዴ እጁን በበሩ ቀዳዳ አሾለከ፤ ልቤም ስለ እርሱ ይታወክ ጀመር። ለውዴ ልከፍትለት ተነሣሁ፤ በከርቤ ነጠብጣብ የራሱት እጆቼ፣ በከርቤም ፈሳሽ የተነከሩት ጣቶቼ፣ የመወርወሪያውን እጀታ ያዙ። ለውዴ ከፈትሁለት፤ ውዴ ግን አልነበረም፤ ሄዷል፤ በመሄዱም ልቤ ደነገጠ፤ ፈለግሁት፤ ነገር ግን አላገኘሁትም፤ ጠራሁት፤ ነገር ግን አልመለሰልኝም። የከተማዪቱም ጠባቂዎች፣ በከተማዪቱ ውስጥ ሲዘዋወሩ አገኙኝ፤ እነዚህ የቅጥሩ ጠባቂዎች፣ ደበደቡኝ፤ አቈሰሉኝ፤ ልብሴንም ገፈፉኝ። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፤ እማጠናችኋለሁ፤ ውዴን ካገኛችሁት፣ ምን ትሉት መሰላችሁ? በፍቅሩ መታመሜን ንገሩት። አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ ሆይ፤ ውድሽ ከሌሎች እንዴት ቢበልጥ ነው? እስከዚህ የምትማጠኚንስ፣ ውድሽ ከሌሎች እንዴት ቢበልጥ ነው? ውዴ ፍልቅልቅና ደመ ግቡ ነው፤ ከዐሥር ሺሖችም የሚልቅ ነው። ራሱ የጠራ ወርቅ፣ ጠጕሩ ዞማ፣ እንደ ቍራም የጠቈረ ነው። ዐይኖቹ፣ በጅረት አጠገብ እንዳሉ ርግቦች፣ በወተት የታጠቡ፣ እንደ ዕንቍም ጕብ ጕብ ያሉ ናቸው። ጕንጮቹ የሽቱ መዐዛ የሚያመጡ፣ የቅመማ ቅመም መደቦችን ይመስላሉ፤ ከንፈሮቹም ከርቤ እንደሚያንጠባጥቡ፣ ውብ አበቦች ናቸው። ክንዶቹ በቢረሌ ፈርጥ ያጌጠ፣ የወርቅ ዘንግን ይመስላሉ፤ ሰውነቱም በሰንፔር ፈርጥ ያጌጠ፣ አምሮ የተሠራ የዝኆን ጥርስን ይመስላል። እግሮቹ በንጹሕ ወርቅ መቆሚያ ላይ የተተከሉ፣ የዕብነ በረድ ምሰሶዎችን ይመስላሉ፤ መልኩ እንደ ሊባኖስ ነው፤ እንደ ዝግባ ዛፎቹም ምርጥ ነው። አፉ ራሱ ጣፋጭ ነው፤ ሁለንተናውም ያማረ ነው። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፤ ውዴ ይህ ነው፤ ባልንጀራዬም እርሱ ነው።