መጽ​ሐፈ ሲራክ 11

11
1ድሃ በጥ​በቡ ይከ​ብ​ራል፤
በመ​ኳ​ን​ን​ትም መካ​ከል ይቀ​መ​ጣል።
2ስለ መልከ መል​ካ​ም​ነቱ ለሰው አታ​ድላ፤
ስለ መልከ ጥፉ​ነ​ቱም ሰውን አት​ና​ቀው።
3ንብ ከወ​ፎች ሁሉ ታን​ሳ​ለች፤
ማርዋ ግን ከሁሉ ይጣ​ፍ​ጣል።
4በል​ብ​ስህ ጌጥ አት​ታ​በይ።
በከ​በ​ር​ህ​በ​ትም ወራት ራስ​ህን አታ​ኵራ።
የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሥራው ልዩ፥ ጥበ​ቡም ከሰው የተ​ሰ​ወረ ነውና።
5በም​ድር የወ​ደቁ መኳ​ን​ንት ብዙ ናቸው፤
ዘውድ የተ​ቀ​ዳጀ ባሕ​ታ​ዊም አለ።
6ፈጽ​መው የተ​ዋ​ረዱ መኳ​ን​ንት ብዙ ናቸው፤
በሌ​ሎ​ችም እጅ የወ​ደቁ መኳ​ን​ንት ብዙ ናቸው።
7ሳት​መ​ረ​ምር አት​ን​ቀፍ፤
አስ​ቀ​ድ​መህ ተረዳ፥ በኋ​ላም ትቈ​ጣ​ለህ።
8ሳት​ሰማ አት​መ​ልስ፤
በሌ​ላ​ውም ነገር ውስጥ አት​ግባ።
9ግዳ​ጅ​ህም ባል​ሆነ ነገር አት​ጨ​ነቅ፤
ከኀ​ጢ​አ​ተ​ኞች ጋርም በፍ​ርድ አት​ቀ​መጥ።
10ልጄ ሆይ፥ ሥራ​ህን አታ​ብዛ፤ ብታ​በዛ ትከ​ብር ዘንድ አያ​ሠ​ለ​ጥ​ን​ህ​ምና፤
ብት​ሮጥ አታ​መ​ል​ጥም፥ ብት​ከ​ተ​ልም አታ​ገ​ኝም።
11የሚ​ቸ​ኩ​ልና የሚ​ሠራ፥ የሚ​ደ​ክ​ምም አለ፤
ነገር ግን እጅግ ይቸ​ገ​ራል።
12ደክሞ ሳለም የማ​ይ​ለ​ምን፥ ምንም ማድ​ረግ ሳይ​ችል የሚ​ገዛ አለ፤
ምንም ቢጸና ፈጽሞ የሚ​ቸ​ገር አለ።
13እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን በመ​ል​ካም ዐይን ቢያ​የው ከች​ግሩ ያነ​ሣ​ዋል።#ምዕ. 11 ቍ. 12 በግ​ሪክ ሰባ. ሊ. “ዳግ​መኛ ሌላ ደካማ ርዳ​ታም የሚ​ያ​ስ​ፈ​ል​ገው ችሎ​ታም የሌ​ለው ድህ​ነ​ት​ንም የተ​ሞላ አለ፥ ነገር ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በመ​ል​ካም ያየ​ዋል። ከች​ግ​ሩም ያነ​ሣ​ዋል” ይላል።
ከፍ ከፍ ያደ​ር​ገ​ዋል፥ ያከ​ብ​ረ​ዋል፥ ብዙ ሰዎ​ችም ያደ​ን​ቁ​ታል።
14መል​ካ​ምና ክፉ፥ ሕይ​ወ​ትና ሞት፤
ድህ​ነ​ትና ብል​ጽ​ግና ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ናቸው።
15ጥበብ፥ ማስ​ተ​ዋ​ልና ሕግን ማወቅ፥
ፍቅ​ርና መል​ካም ሥራን መሥ​ራት ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ይመ​ጣሉ።
16ስሕ​ተ​ትና ጨለማ ከመ​ወ​ለ​ዳ​ቸው ጀምሮ ከኃ​ጥ​ኣን ጋር ኖረ​ዋል።
ክፋ​ትም በእ​ርሱ ደስ ከሚ​ሰ​ኙት ጋር አብሮ ያድ​ጋል።
17የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጸጋው ጻድ​ቃ​ንን ትጠ​ብ​ቃ​ቸ​ዋ​ለች፤
ፈቃ​ዱም ለዘ​ለ​ዓ​ለም ደስ ታሰ​ኛ​ለች።
18እየ​ነ​ፈገ በን​ፍ​ገቱ ብዛት የሚ​ከ​ብር ሰው አለ።
በእ​ር​ስ​ዋም ደስ​ታ​ውን ይፈ​ጽ​ም​ባ​ታል።
19ያርፍ ዘንድ ተስፋ ባደ​ረገ ጊዜ፥
“እበ​ላ​ለሁ እጠ​ጣ​ለሁ፥ እን​ግ​ዲ​ህስ ደስ ይለ​ኛል፥ በቃ​ኝም” ባለ ጊዜ፥
የሚ​ሞ​ት​ባ​ትን ቀን አያ​ው​ቅም፤
ገን​ዘ​ቡ​ንም ሁሉ ለባ​ዕድ ትቶ እርሱ ይሞ​ታል።
20በቃል ኪዳ​ንህ ቁም፤ በእ​ር​ሱም ተማር፤
በሥ​ራ​ህም ሸም​ግል።
21የኀ​ጢ​አ​ተ​ኞች ሥራ​ቸው አያ​ስ​ጐ​ም​ጅህ፥
በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እመን፥ ድካ​ም​ህ​ንም ተስፋ አድ​ርግ፥
ሁሉ በአ​ንድ ጊዜ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ቀሊል ነውና፥
ድሃ​ው​ንም ድን​ገት ያከ​ብ​ረ​ዋ​ልና።
22የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በረ​ከት ለጻ​ድ​ቃን ዋጋ​ቸው ናት፥
የጻ​ድ​ቅም በረ​ከቱ ትበ​ዛ​ለች።
23“የአ​ገ​ል​ግ​ሎቴ ትርፍ ምን​ድን ነው?
ከእ​ን​ግ​ዲ​ህስ ወዲያ የማ​ገ​ኘው መል​ካም ነገር ምን​ድን ነው?” አት​በል።
24“እን​ግ​ዲ​ህስ በቃኝ፥
ከእ​ን​ግ​ዲ​ህም ወዲያ አል​ቸ​ገ​ርም” አት​በል።
25በመ​ል​ካም ቀን ጊዜ ክፉ ይረ​ሳል፤
በክፉ ቀንም ጊዜ መል​ካም ይረ​ሳል።
26የሞት ቀን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ቀሊል ነው፤
ለሰው እንደ ሥራው ዋጋ​ውን ይከ​ፍ​ለ​ዋ​ልና።
27በክፉ ቀን ጥጋብ ያቀ​ና​ጣል፤
የሰ​ውም ሥራው በፍ​ጻሜ ዘመኑ ይታ​ወ​ቃል።
28ፍጻ​ሜ​ውን ሳታይ ሰውን ብፁዕ አት​በ​ለው፥
የሰው አኗ​ኗሩ በል​ጆቹ ይገ​ለ​ጣል።
ጓደ​ኛን ስለ መም​ረጥ
29ተን​ኰ​ለኛ ብዙ ይተ​ነ​ኰ​ል​ብ​ሃ​ልና
ያገ​ኘ​ኸ​ውን ሰው ሁሉ ወደ ቤትህ አታ​ግባ።
30ቆቅ በወ​ጥ​መድ ይያ​ዛል፥
የት​ዕ​ቢ​ተኛ ሰውም ልቡ እን​ደ​ዚሁ ነው፤
መከ​ራ​ው​ንም እንደ ጕበኛ ይመ​ለ​ከ​ታ​ታል።
31ተን​ኰ​ለኛ ሰው በበጎ ፋንታ ክፉ ነገ​ርን ይከ​ፍ​ል​ሃል፤
ሳይ​ኖ​ር​ብህ ነው​ርን ያወ​ጣ​ብ​ሃል።
32በእ​ሳት ትን​ታግ ብዛት ፍሙ ይበ​ዛል፤
ኀጢ​አ​ተኛ ሰውም ሰው​ነ​ቱን ያድ​ድ​ና​ታል።
33ክፉ ነገ​ርን ይሠ​ራ​ብ​ሃ​ልና፥
ሁል​ጊዜ ስድ​ብን እን​ዳ​ያ​ደ​ር​ግ​ብህ ከክፉ ሰው ተጠ​በቅ።
34ባዕድ ሰውን ከአ​ንተ ጋር ብታ​ሳ​ድር ያው​ክ​ሃል፤
ይወ​ነ​ጅ​ል​ሃል፥ ከገ​ን​ዘ​ብ​ህም ይለ​ይ​ሃል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ