መጽሐፈ ሲራክ 10
10
1ጠቢብ ንጉሥ ሕዝቡን ይመክራል፥
አስተዋይ ዳኛም ሥርዐትን ይሠራል።
2ሎሌውም እንደ ሕዝቡ አለቃ ነው፤
የከተማው ገዥ እንደሚሠራው በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ይሠራሉ።
3አላዋቂ ንጉሥ ሕዝቡን ያጠፋል፤
ሀገርም በሽማግሌዎች ጥበብ ትጸናለች።
4የምድር ግዛት በእግዚአብሔር እጅ ነው፥
በጊዜውም የሚጠቅመውን ሰው በእርስዋ ላይ ያስነሣል።
5የሰው በረከቱ በእግዚአብሔር እጅ ነው፥
በጸሓፊም ሰውነት ክብሩን ያኖራል።
በትዕቢት የሚመጣ ኀጢአት
6ባልንጀራህን በሳተበት ሁሉ አትንቀፈው፥
በነቀፋህም ምንም ክፉ ነገር የምታደርግበት አይኑር።
7ትዕቢት በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ የተጠላ ነው፥
ከሁሉም ዐመፅ ትከፋለች።
8መንግሥትም ስለ ዐመፅና ክርክር፥ ስለ ገንዘብም፥
ካንዱ ወገን ወደ ሌላው ወገን ትፈልሳለች።
9እንግዲህ ትቢያና ዐመድ የሚሆን፥
በሕይወትም ሳለ ሰውነቱ የሚተላ ሰው ለምን ይታበያል?
10የሰፋ ቍስልን ባለ መድኀኒት ያድነዋል፤
ንጉሥ መባል ግን ለዛሬ ብቻ ነው፥ ነገም ይሞታል።
11ሰውም ከሞተ በኋላ የትል ዕድል ፋንታ ይሆናል።
12የትዕቢት መጀመሪያ ሰውን ከእግዚአብሔር ትለየዋለች፤
ልቡናውንም ከፈጣሪው ታርቀዋለች።
13ትዕቢት የኀጢአት መጀመሪያ ናት፤
በአጸናትም ሰው ላይ ርኵሰትን ታበዛበታለች፥
ስለዚህም እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ፍዳ ይገልጣል፥
ፈጽሞም ያጠፋቸዋል።
14እግዚአብሔር ያለቆችን ዙፋን ያፈርሳል፤
በእነርሱም ፋንታ የዋሃንን ይሾማል።
15እግዚአብሔር የአሕዛብን ሥራቸውን ነቀለ፥
በእነርሱም ፋንታ ትሑታንን ተከለ።
16እግዚአብሔር የአሕዛብን ሀገሮች አጠፋ፥
እስከ ምድር መሠረት ድረስ አጠፋቸው።
17ፈጽሞም አጠፋቸው፥
ስም አጠራራቸውንም ከምድር ደመሰሰ።
18ትዕቢት ለሰው የተፈጠረ አይደለም፥
ቍጣና ጥፋትም ከሴት ለሚወለድ ሰው አይደለም።
ክብር ስለሚገባቸውና ስለማይገባቸው
19የሰው ዘር የከበረ ዘር ነው፥
የከበረ ዘር ማንነው? እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ዘር አይደለምን?
20የሰው ዘር የጐሰቈለ ዘር ነው፥
ጐስቋላው ዘር ማንነው? የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የማይጠብቁ ሰዎች ዘር አይደለምን?
21ዳኛ ከባልንጀራው ይልቅ የከበረ ነው፥
እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ግን ከእርሱ ይልቅ ይከብራሉ።
22ለባለጸጋውና ለከበርቴው ለድሃውም
ክብራቸው እግዚአብሔርን መፍራት ነው።
23ድሃውን ስለ ድህነቱ ይንቁት ዘንድ አይገባም፥
ኀጢአተኛውንም ሰው ስለ ባለጸግነቱ ያከብሩት ዘንድ አይገባም።
24ታላላቆችና አለቆች፥ መኳንንቱም ይከብራሉ፤
ከእነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን የሚበልጠው የለም።
25ጠቢብ ቤተ ሰብ በንጹሕ ያገለግላል፥
ዐዋቂ ሰውም አይነቅፈውም።
26ሥራህን ስትሠራ አትራቀቅ፥
በችግርህም ወራት አትመካ።
27ከሚዞርና ከሚመካ፥ ምግቡንም ከማያገኝ ሰው ይልቅ፥
የሚያርስና የሚቈፍር ይሻላል።
28ልጄ ሆይ፥ በየዋህነትህ ሰውነትህን ደስ አሰኛት፥
የተቻለህንም ያህል አዘጋጃት።
29ለራሱ የሚነፍግ ለማን ቸር ይሆናል?#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በራሱ ኀጢአት የሚሠራን ሰው ማን ንጹሕ ያደርገዋል? ራሱን የሚያዋርደውንስ ማን ያከብረዋል” ይላል።
ሰውነቱን የማያዘጋጃትን ሰውስ ማን ያመሰግነዋል?
30ድሃውን ስለ ጥበቡ ያመሰግኑታል፥
ባለጠጋውን ግን ስለ ባለጠግነቱ ያመሰግኑታል።
31በተቸገረ ጊዜ የማያዝን ሰው፥
በተዘጋጀ ጊዜ እንዴት ደስ ይለው?#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በተቸገረ ጊዜ የተከበረ ሰው በበለጸገ ጊዜ ምን ያህል ይከብር ይሆን? በበለጸገበት ጊዜ የተዋረደስ በተቸገረ ጊዜ ምን ያህል ይዋረድ ይሆን?” ይላል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 10: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ