መጽሐፈ ሲራክ 11
11
1ድሃ በጥበቡ ይከብራል፤
በመኳንንትም መካከል ይቀመጣል።
2ስለ መልከ መልካምነቱ ለሰው አታድላ፤
ስለ መልከ ጥፉነቱም ሰውን አትናቀው።
3ንብ ከወፎች ሁሉ ታንሳለች፤
ማርዋ ግን ከሁሉ ይጣፍጣል።
4በልብስህ ጌጥ አትታበይ።
በከበርህበትም ወራት ራስህን አታኵራ።
የእግዚአብሔር ሥራው ልዩ፥ ጥበቡም ከሰው የተሰወረ ነውና።
5በምድር የወደቁ መኳንንት ብዙ ናቸው፤
ዘውድ የተቀዳጀ ባሕታዊም አለ።
6ፈጽመው የተዋረዱ መኳንንት ብዙ ናቸው፤
በሌሎችም እጅ የወደቁ መኳንንት ብዙ ናቸው።
7ሳትመረምር አትንቀፍ፤
አስቀድመህ ተረዳ፥ በኋላም ትቈጣለህ።
8ሳትሰማ አትመልስ፤
በሌላውም ነገር ውስጥ አትግባ።
9ግዳጅህም ባልሆነ ነገር አትጨነቅ፤
ከኀጢአተኞች ጋርም በፍርድ አትቀመጥ።
10ልጄ ሆይ፥ ሥራህን አታብዛ፤ ብታበዛ ትከብር ዘንድ አያሠለጥንህምና፤
ብትሮጥ አታመልጥም፥ ብትከተልም አታገኝም።
11የሚቸኩልና የሚሠራ፥ የሚደክምም አለ፤
ነገር ግን እጅግ ይቸገራል።
12ደክሞ ሳለም የማይለምን፥ ምንም ማድረግ ሳይችል የሚገዛ አለ፤
ምንም ቢጸና ፈጽሞ የሚቸገር አለ።
13እግዚአብሔር ግን በመልካም ዐይን ቢያየው ከችግሩ ያነሣዋል።#ምዕ. 11 ቍ. 12 በግሪክ ሰባ. ሊ. “ዳግመኛ ሌላ ደካማ ርዳታም የሚያስፈልገው ችሎታም የሌለው ድህነትንም የተሞላ አለ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር በመልካም ያየዋል። ከችግሩም ያነሣዋል” ይላል።
ከፍ ከፍ ያደርገዋል፥ ያከብረዋል፥ ብዙ ሰዎችም ያደንቁታል።
14መልካምና ክፉ፥ ሕይወትና ሞት፤
ድህነትና ብልጽግና ከእግዚአብሔር ዘንድ ናቸው።
15ጥበብ፥ ማስተዋልና ሕግን ማወቅ፥
ፍቅርና መልካም ሥራን መሥራት ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣሉ።
16ስሕተትና ጨለማ ከመወለዳቸው ጀምሮ ከኃጥኣን ጋር ኖረዋል።
ክፋትም በእርሱ ደስ ከሚሰኙት ጋር አብሮ ያድጋል።
17የእግዚአብሔር ጸጋው ጻድቃንን ትጠብቃቸዋለች፤
ፈቃዱም ለዘለዓለም ደስ ታሰኛለች።
18እየነፈገ በንፍገቱ ብዛት የሚከብር ሰው አለ።
በእርስዋም ደስታውን ይፈጽምባታል።
19ያርፍ ዘንድ ተስፋ ባደረገ ጊዜ፥
“እበላለሁ እጠጣለሁ፥ እንግዲህስ ደስ ይለኛል፥ በቃኝም” ባለ ጊዜ፥
የሚሞትባትን ቀን አያውቅም፤
ገንዘቡንም ሁሉ ለባዕድ ትቶ እርሱ ይሞታል።
20በቃል ኪዳንህ ቁም፤ በእርሱም ተማር፤
በሥራህም ሸምግል።
21የኀጢአተኞች ሥራቸው አያስጐምጅህ፥
በእግዚአብሔር እመን፥ ድካምህንም ተስፋ አድርግ፥
ሁሉ በአንድ ጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ቀሊል ነውና፥
ድሃውንም ድንገት ያከብረዋልና።
22የእግዚአብሔር በረከት ለጻድቃን ዋጋቸው ናት፥
የጻድቅም በረከቱ ትበዛለች።
23“የአገልግሎቴ ትርፍ ምንድን ነው?
ከእንግዲህስ ወዲያ የማገኘው መልካም ነገር ምንድን ነው?” አትበል።
24“እንግዲህስ በቃኝ፥
ከእንግዲህም ወዲያ አልቸገርም” አትበል።
25በመልካም ቀን ጊዜ ክፉ ይረሳል፤
በክፉ ቀንም ጊዜ መልካም ይረሳል።
26የሞት ቀን በእግዚአብሔር ዘንድ ቀሊል ነው፤
ለሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ይከፍለዋልና።
27በክፉ ቀን ጥጋብ ያቀናጣል፤
የሰውም ሥራው በፍጻሜ ዘመኑ ይታወቃል።
28ፍጻሜውን ሳታይ ሰውን ብፁዕ አትበለው፥
የሰው አኗኗሩ በልጆቹ ይገለጣል።
ጓደኛን ስለ መምረጥ
29ተንኰለኛ ብዙ ይተነኰልብሃልና
ያገኘኸውን ሰው ሁሉ ወደ ቤትህ አታግባ።
30ቆቅ በወጥመድ ይያዛል፥
የትዕቢተኛ ሰውም ልቡ እንደዚሁ ነው፤
መከራውንም እንደ ጕበኛ ይመለከታታል።
31ተንኰለኛ ሰው በበጎ ፋንታ ክፉ ነገርን ይከፍልሃል፤
ሳይኖርብህ ነውርን ያወጣብሃል።
32በእሳት ትንታግ ብዛት ፍሙ ይበዛል፤
ኀጢአተኛ ሰውም ሰውነቱን ያድድናታል።
33ክፉ ነገርን ይሠራብሃልና፥
ሁልጊዜ ስድብን እንዳያደርግብህ ከክፉ ሰው ተጠበቅ።
34ባዕድ ሰውን ከአንተ ጋር ብታሳድር ያውክሃል፤
ይወነጅልሃል፥ ከገንዘብህም ይለይሃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 11: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ