የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮ​ሐ​ንስ ራእይ 8

8
ሰባተኛው ማኅተምና የወርቁ ማዕጠንት
1ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ግማሽ ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። 2በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። 3ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። 4የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ። 5መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት፤ ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ።
ሰባቱ መለከቶች
6ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ።
7ፊተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፤ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ፤ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።
8ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ፤ 9በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ።
10ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞችና በውሃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። 11የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፤ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፤ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ።
12አራተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፤ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።
13አየሁም፤ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ “ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” ሲል ሰማሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ