የዮሐንስ ራእይ 7
7
በእግዚአብሔር ማኅተም ስለታተሙ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች
1ከዚህም በኋላ በአራቱ የምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ፤ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ። 2የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፤ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ 3“የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ፤” አላቸው። 4የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። 5ከይሁዳ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፤ ከሮቤል ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ 6ከአሴር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከምናሴ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ 7ከስምዖን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ 8ከዛብሎን ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።
ከየነገዱ የተሰበሰቡ ብዙ ሕዝቦች
9ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ 10በታላቅም ድምፅ እየጮሁ
“ማዳን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው የአምላካችንና የበጉ ነው!”
አሉ። 11መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ
12“አሜን በረከትና ገናናነት ጥበብም ምስጋናም ክብርም
ኀይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን
ይሁን! አሜን።”
አሉ።
13ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ “እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ?” አለኝ። 14እኔም “ጌታ ሆይ! አንተ ታውቃለህ፤” አልሁት። አለኝም “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ። 15ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፤ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል። 16ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፤ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤ 17በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ