መጽሐፈ ምሳሌ 21
21
1የንጉሥ ልብ እንደ ውኃ ፈሳሽ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤
ወደ ወደደውም ይመልሳታል፥
በዚያም ትቈያለች።#በዕብ የለም።
2ሰው ሁሉ ለራሱ ጻድቅ መስሎ ይታያል፤
እግዚአብሔር ግን ልብን ያቀናል።
3ጽድቅንና ቅን ፍርድን ማድረግ
መሥዋዕት ከመሠዋት ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው።
4ለስድብ በልብ አለመቸኮል ታላቅ ዕውቀት ነው
የኃጥኣንም ብርሃናቸው ኀጢአት ነው።
5የትጉህ ዐሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል፥
ችኩል ሰው ሁሉ ግን ለመጕደል ይቸኩላል።#በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በግእዝ የለም።
6በሐሰተኛ ምላስ ሀብትን የሚያከማች ከንቱ ነገርን ይከተላል፥
ወደ ሞት ወጥመድም ያደርሰዋል።
7ጽድቅን ያደርጉ ዘንድ አይወድዱምና
የኃጥኣን ጥፋት ከሩቅ ይመጣል።
8እግዚአብሔር ለጠማሞች ጠማማ ሥራን ይልክባቸዋል፤
ሥራው የቀናና ንጹሕ ነውና።
9ከነዝናዛ ሴት ጋር በተለሰነ ቤት ከመቀመጥ ይልቅ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከነዝናዛ ሴት ጋር” አይልም።
ከቤት ውጭ በማዕዘን ላይ መቀመጥ ይሻላል።
10የኀጢአተኛ ነፍስ በአንድ ሰው እንኳ ይቅር አትባልም።
11ክፉ ሰው ሲዋረድ የዋህ ሰው ዐዋቂ ይሆናል፤
ጥበብን የሚረዳ ሰውም ዕውቀትን ይቀበላል።
12የክፉዎች ልብ ጽድቅን አያውቅም፥
ክፋትም ኃጥአንን ያከፋቸዋል።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ጻድቅ የክፉዎችን ልብ ያውቃል ክፉዎችንም ስለ ኀጢአታቸው ይነቅፋቸዋል” ይላል።
13ድሃን እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥
እርሱ ራሱ ይጣራል፥ የሚሰማውም የለም።
14በስውር ያለ ስጦታ ቍጣን ይመልሳል፥
ስጦታን የሚሸልግ ግን ጽኑ ቍጣን ያስነሣል።
15ፍርድን ማድረግ ለጻድቃን ደስታ ነው፤
ጻድቅ ሰው ግን ክፉ በሚሠሩ ዘንድ የረከሰ ነው።
16ከጽድቅ መንገድ የሚሳሳት ሰው፥
በረዐይት ጉባኤ ያርፋል።
17ደስታን የሚወድድ ድሃን ይሆናል፥
የወይን ጠጅንና ዘይትን የሚወድድም ባለጠጋ አይሆንም።
18ኃጥእ በጻድቅ ዘንድ የተናቀ ነው፥
ኃጥእም የጻድቅ ቤዛ ነው።#በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ ሁለተኛው መስመር የለም።
19ከቍጡ፥ ከነዝናዛና ከነገረኛ ሴት ጋር ከመቀመጥ ይልቅ
በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል።
20የተወደደ መዝገብ በጠቢባን አፍ ያርፋል፤
አላዋቂዎች ግን ያጡታል።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ይውጡታል” ይላል።
21ጽድቅንና ምሕረትን የሚከተል
ሕይወትንና ክብርን ያገኛል።
22ጠቢብ የጸናች ከተማን ይገባባታል፥
ክፉዎች የሚተማመኑበትንም ኀይል ያፈርሳል።
23አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ
ነፍሱን ከመከራ ይጠብቃል።
24የችኩል፥ የነዝናዛና የነገረኛ ሰው ስሙ ቸነፈር ነው፥
ክፉን የሚያስብም ኃጥእ ነው።
25ታካችን ምኞቱ ትገድለዋለች፥
እጆቹ ምንም ይሠሩ ዘንድ አይፈቅዱምና።
26ኃጥእ ቀኑን ሁሉ ክፉ ምኞትን ይመኛል፥
ጻድቅ ግን ዐውቆ ይራራል፥ ይመጸውታልም።
27የኃጥኣን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፥
በክፋት ያቀርቡታልና።
28ሐሰተኛ ምስክር ይጠፋል፤
የሚሰማ ሰው ግን ተጠንቅቆ ይናገራል።
29ኃጥእ ሰው ያለ ኀፍረት ፊት ለፊት ይቃወማል፤
ቅን ሰው ግን መንገዱን ይረዳል።
30ጥበብና ብርታት፥ ምክርም፥
በኃጥእ ዘንድ የሉም።
31ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤
ረድኤት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 21: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ