የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 20

20
1ለተሳዳቢና ለሰካራም ወይን ክፉ ነው፥
ጽዋውንም መላልሶ የሚጨልጥ ጠቢብ አይደለም፥
እንደዚህ ያለ አላዋቂም ሁሉ አንድ ይሆናል።
2የንጉሥ ቍጣ ከአንበሳ ቍጣ አያንስም፤
የሚያስቈጣውም ሰው የራሱን ነፍስ ይበድላል።
3የሰው ክብሩ ከስድብ መከልከል ነው፤
ሰነፍ ሁሉ ግን እንዲህ ባለ ነገር ይጣመራል።
4ታካች ሰው ሲያሽሟጥጡት አያፍርም፤
ስለዚህ በመከር ጊዜ ይለምናል፥ የሚሰጠውም የለም።
በክምሩ እያለ ስንዴ የሚበደር እንደዚሁ ነው።#በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
5ምክር በሰው ልብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤
አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።
6ይቅር ባይ ሰው ታላቅና ክቡር ነው፤
ነገር ግን የታመነ ሰው የሚገኘው በድካም ነው።
7ያለ ነውር ወደ እውነት በንጹሕ የሚሄድ፥
ልጆቹን ብፁዓን ያደርጋቸዋል።
8እውነተኛ ንጉሥ በዙፋኑ በተቀመጠ ጊዜ
በዐይኖቹ ፊት ምንም ክፉ አይቃወመውም።
9ንጹሕ ልብ አለኝ ብሎ የሚመካ ማን ነው?
ከኀጢአትስ ንጹሕ ሆኖ የሚታይ ማን ነው?
10ሁለት ዐይነት ሚዛንና ሁለት ዐይነት መስፈሪያ፥
ሁለቱ በእግዚአብሔር ፊት ርኩሳን ናቸው።
የሚሠራቸውም በሥራው ይሰነካከላል።
11የእውነተኛ ጐልማሳ መንገዱ የቀና ነው።
12የሚሰማ ጆሮና የሚያይ ዓይን፥
ሁለቱ የእግዚአብሔር ሥራ ናቸው።
13እንዳትወገድ ማማትን አትውደድ።
ድሃም እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ
ዐይንህን ክፈት፥ እንጀራም ትጠግባለህ።
14የሚገዛ ሰው፦ “ክፉ ነው፥ ክፉ ነው” ይላል፤
በሄደ ጊዜ ግን ይመካል።
15ወርቅና ብዙ ቀይ ዕንቍ ይገኛል፤
የዕውቀት ከንፈር ግን የከበረች ጌጥ ናት።
16ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥
ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው።
17የሐሰት እንጀራ ለሰው የጣፈጠ ነው፤
ከዚህ በኋላ ግን አፉ ጭንጫ ይሞላል።
18ዐሳብ በምክር ትጸናለች፥
በመልካምም ምክር ሰልፍ አድርግ።
19ዘዋሪ ሐሜተኛ ምሥጢርን ይገልጣል፤
በከንፈሩ የሚያባብል ሰውን አትገናኘው።#ምዕ. 20 ከቍ. 14 እስከ 19 በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በግእዝ የሉም።
20አባቱንና እናቱን የሚያማ ብርሃኑ ይጠፋል፥
የዐይኖቹ ብሌንም ጨለማን ያያል።
21አስቀድሞ ለርስት የሚቸኩል፥
በፍጻሜው አይባረክም።
22ጠላቴን እበቀለዋለሁ አትበል፤
ነገር ግን እንዲረዳህ እግዚአብሔርን ተማመን።
23ሁለት ዓይነት ሚዛን በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፥
ሐሰተኛ ሚዛንም መልካም አይደለም።
24የሰው አካሄዱ በእግዚአብሔር ዘንድ ይቃናል፤
ሟች ግን መንገዱን እንዴት ያውቃል?
25ሰው ከገንዘቡ በችኮላ የተቀደሰ ነው ብሎ ቢሳል፥
ከተሳለም በኋላ ቢፀፀት ወጥመድ ይሆንበታል።
26ብልህ ንጉሥ የኃጥኣን መንሽ ነው፥
በእነርሱ ላይም መንኰራኵርን ይነዳባቸዋል።
27የሰው መንፈስ የሆድን መዛግብት የሚመረምር፥
የእግዚአብሔር መብራት ነው።
28ቸርነትና እውነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤
ዙፋኑንም በእውነት ይከቡታል።
29ለጐልማሶች ጌጣቸው ጥበብ ነው።
ለሽማግሌዎችም ክብራቸው ሽበት ነው።
30ሽብርና ስደት ክፉዎችን ድንገት ይገናኛቸዋል፥
ግርፋትም ወደ ሆድ ዕቃ ይገባል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ