ትንቢተ አብድዩ 1
1
በኤዶምያስ ላይ የሚደርስ ቅጣት
1የአብድዩ ራእይ።
ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከእግዚአብሔር ዘንድ መስማትን ሰማሁ፤ ከባቢን ወደ አሕዛብ ልኮ፥ “ተነሡ፤ በላይዋም እንነሣና እንውጋት። 2እነሆ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፤ አንተ እጅግ ተንቀሃል። 3በተሰነጠቀም ዓለት ውስጥ እንደሚኖር- ማደሪያውንም ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ፥ በልቡም፦ ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? እንደሚል፥ የልብህ ትዕቢት እጅግ አኵርቶሃል። 4እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር።
5“ሌቦች ቢመጡብህ፥ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን የሚሰርቁ አይደሉምን? ወይንም የሚቈርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ አያስቀሩምን? 6ዔሳውን እንዴት መረመሩት! የሸሸገውንም እንዴት ወሰዱበት! 7የተማማልሃቸው ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፤ የተስማሙህም ሰዎች ተነሡብህ፤ አሸነፉህም፤ በበታችህም አሽክላ ዘረጉብህ፤ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም። 8በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳው ተራራም ማስተዋልን አጠፋለሁ ይላል እግዚአብሔር። 9ከዔሳው ተራራ ሰዎች ሁሉ ይጠፉ ዘንድ የቴማን ሰልፈኞችህ ይደነግጣሉ።
10“በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለ ተደረገ ኀጢአትና ግድያ ኀፍረት ይከድንሃል፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ። 11በፊቱ አንጻር በቆምህ ቀን፥ አሕዛብ ጭፍራውን በማረኩበት፥ እንግዶችም በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተ ደግሞ ከእነርሱ እንደ አንዱ ነበርህ። 12በጠላት ቀን ወንድምህን ዝቅ አድርገህ ትመለከተው ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች ላይ ደስ ይልህ ዘንድ፥ በጭንቀታቸውም ቀን በትዕቢት ትናገር ዘንድ ባልተገባህ ነበር። 13በችግራቸውም ቀን በሕዝቤ በር ትገባ ዘንድ፥ በጥፋታቸውም ቀን ጉባኤያቸውን ትመለከት ዘንድ፥ በእልቂታቸውም ቀን በሠራዊታቸው ላይ አደጋ ትጥል ዘንድ አይገባህም ነበር።#ዕብ. “በሀብታቸው ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ ...” ይላል። 14የሸሹትንም ለማጥፋት በመተላለፊያ መንገዳቸው ትቆም ዘንድ፥ ድል በተነሡበትም ቀን ከእርሱ ያመለጡትን ለማስጨነቅ ትከብባቸው ዘንድ ባልተገባህ ነበር።
እግዚአብሔር በአሕዛብ እንደሚፈርድ
15“የእግዚአብሔር ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቦአልና፥ አንተ እንደ አደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፤ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል። 16በቅዱሱ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣህ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ወይንን ይጠጣሉ፤ አዎን፥ ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፤ እንዳልነበሩም ይሆናሉ።
የእስራኤል ድል
17“ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ መድኀኒት ይሆናል፤ እርሱም ቅዱስ ይሆናል፤ የያዕቆብም ቤት ሰዎች የወረሱአቸውን ይወርሳሉ። 18እግዚአብሔርም ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍም ቤት ነበልባል፥ የዔሳውም ቤት ገለባ ይሆናሉ፤ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል፤ ይበሉአቸውማል፤ ከዔሳውም ቤት ቅሬታ አይኖርም። 19የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቆላውም ሰዎች ፍልስጥኤማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም ተራራ፥ የሰማርያን፥ የብንያምንና የገለዓድን ሀገር ይወርሳሉ።#ዕብ. “ብንያም ገለዓድን ይወርሳል” ይላል። 20ይህም የእስራኤል ልጆች የጭፍራቸው#“የጭፍራቸው” የሚለው በዕብ. ብቻ። ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፤ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች እስከ ኤፍራታ ድረስ የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ። 21የዳኑትም የዔሳውን ተራራ ይበቀሉት ዘንድ ከጽዮን ተራራ ይዘምታሉ፤ መንግሥትም ለእግዚአብሔር ይሆናል።”
Currently Selected:
ትንቢተ አብድዩ 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ