“ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የምስክሩን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ፤ ታነጻቸውማለህ፤ ስጦታም አድርገህ በፊቴ ታቀርባቸዋለህ። እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ መጀመሪያ በሚወለድ ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ። በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው። በእስራኤልም ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ። ሌዋውያንንም ስጦታ አድርጌ አገባኋቸው፤ ልዩ በሆነች ድንኳን ውስጥ የእስራኤልን ልጆች ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች ኀጢአት ያቃልሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ተሰጡ፤ ከእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደስ የሚቀርብ አይኑር።” ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው። ሌዋውያንም ከኀጢአት ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፤ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው። ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ ገቡ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው፤ ከሃያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በምስክሩ ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ። ከአምሳ ዓመት በኋላ ከሥራው ይሰናበት። ከዚያም ወዲያ እርሱ አያገልግል። ወንድሙንም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ያገልግል፤ ሰሞናቸውንም ይጠብቅ። ነገር ግን አገልግሎቱን ይተው። እንዲሁ በየሰሞናቸው ለሌዋውያን ታደርጋለህ።”
ኦሪት ዘኍልቍ 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኍልቍ 8:15-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች