እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ ለሕዝቡ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፤ ወደ ምስክሩም ድንኳን አምጣቸው፤ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው። እኔም እወርዳለሁ፤ በዚያም አነጋግርሃለሁ፤ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። ሕዝቡንም በላቸው፦ ሥጋ ማን ያበላናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ በእግዚአብሔር ፊት አልቅሳችኋልና ለነገ ተቀደሱ፤ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፤ ትበሉማላችሁ። አንድ ቀን፥ ወይም ሁለት ቀን፥ ወይም አምስት ቀን፥ ወይም ዐሥር ቀን ወይም ሃያ ቀን አትበሉም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ አወጣኸን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ መርዝም እስኪሆንባችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።” ሙሴም፥ “እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ሥጋን እሰጣቸዋለሁ፥ ወር ሙሉም ይበሉታል አልህ። የበሬና የበግ መንጋ ቢታረድ፥ የባሕር ዓሣ ሁሉ ቢሰበሰብ ይበቃቸዋልን?” አለ። እግዚአሔርም ሙሴን፥ “በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አትችልምን? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይም አይፈጸም እንደ ሆነ እነሆ፥ አንተ ታያለህ” አለው። ሙሴም ወጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔርም በደመናው ወረደ፤ ተናገረውም፤ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተጨመረላቸውም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፤ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ዐረፈባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ፤ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፥ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። የሙሴ ምርጥ ባለሟል የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ ፥ ከልክላቸው” አለው። ሙሴም “የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያሳድር አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” አለው። ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ።
ኦሪት ዘኍልቍ 11 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኍልቍ 11:16-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos