የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 11:16-30

ኦሪት ዘኊልቊ 11:16-30 አማ05

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሕዝብ አመራር በመስጠት የታወቁ ሰባ ሽማግሌዎችን ምረጥ፤ እነርሱንም ሰብስበህ ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣቸውና በአጠገብህ ይቁሙ፤ እኔም ወደዚያ ወርጄ ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፤ ለአንተም ከሰጠሁህ መንፈስ ከፍዬ ለእነርሱ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእነዚህ ሕዝብ ላይ ያለህን ኀላፊነት በመሸከም ይረዱሃል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ይህን ሁሉ ኀላፊነት ብቻህን አትሸከምም። አሁንም ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ለነገ ራሳችሁን አንጹ፤ የምትበሉትም ሥጋ ይኖራችኋል፤ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል ብላችሁ ማልቀሳችሁንና የግብጽ ምድር ይሻለን ነበር ማለታችሁን እግዚአብሔር ሰምቶአል፤ እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እርሱንም ትበላላችሁ። የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ለአምስት፥ ለዐሥር ወይም ለኻያ ቀን ብቻ አይደለም፤ እስኪያንገፈግፋችሁና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ ድረስ አንድ ወር ሙሉ ትመገቡታላችሁ፤ ይህም የሚሆነው እዚህ በመካከላችሁ ያለውን ጌታ ስለ ናቃችሁና፦ ከግብጽ ባልወጣን ኖሮ መልካም ነበር በማለት ስላለቀሳችሁ ነው።’ ” ሙሴም ለእግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ እኔ ስድስት መቶ ሺህ ሕዝብ በመምራት ላይ እገኛለሁ፤ ለአንድ ወር የሚበቃ ሥጋ ልትሰጣቸው ቃል ገብተሃል፤ ታዲያ ምን ያኽል የከብትና የበግ መንጋ ቢታረድ እነርሱን ሊያጠግብ ይችላል? በባሕር ውስጥ ያለው ዓሣ ሁሉ ቢሰበሰብ ለእነርሱ በቂ ሊሆን ይችላልን?” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእኔ የእግዚአብሔር ኀይል ውሱን ነውን? ቃሌ በእናንተ ዘንድ የሚፈጸም ወይም የማይፈጸም መሆኑን አሁን ታያለህ!” ስለዚህ ሙሴ ወጥቶ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ መሪዎች ሰባውን በአንድነት ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ተናገረው፤ ለሙሴ ከሰጠው መንፈስ ከፊሉን ወስዶ በሰባዎቹ መሪዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈስ በወረደባቸውም ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ፤ ይህን ያደረጉት ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነበር። ከተመዘገቡት ከሰባው መሪዎች መካከል ሁለቱ ኤልዳድና ሜዳድ የተባሉት ወደ ድንኳኑ ሳይሄዱ በሰፈር ቈይተው ነበር፤ እዚያው በሰፈር እንዳሉ መንፈስ ወረደባቸውና እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ። አንድ ወጣት ወደ ሙሴ ሲሮጥ ሄዶ “ኤልዳድና ሜዳድ በሰፈር ውስጥ ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ሲል ነገረው። ከጐልማሳነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው!” አለው። ሙሴም “አንተ ስለ እኔ ትቈረቈራለህን? እኔስ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሁሉ ላይ መንፈሱን ቢያወርድና ሁሉም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ቢናገሩ ደስታዬ ነው!” አለው። ሙሴና ሰባዎቹ የእስራኤል መሪዎችም ወደ ሰፈር ተመለሱ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}