ኦሪት ዘኍልቍ 1
1
መጀመሪያው የእስራኤል ሕዝብ ቈጠራ
1እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ በምስክሩ ድንኳን ውስጥ፥ በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን፥ ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ዓመት እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ድምር፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር፥ ወንዱን ሁሉ እያንዳንዱን ቍጠሩ። 3ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን፥ ከእስራኤል ወደ ሰልፍ የሚወጡትን ሁሉ፥ አንተና አሮን በየሠራዊቶቻቸው ቍጠሩአቸው። 4እንደ እየአባቶቻቸው ቤት ከየነገዱ አለቆች አንድ አንድ ሰው ከእናንተ ጋር ይሁን። 5ከእናንተም ጋር የሚቆሙት ሰዎች ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ከሮቤል የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር፥ 6ከስምዖን የሴሩሳዴ ልጅ ሰላምያል፥ 7ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፥ 8ከይሳኮር የሰገር ልጅ ናትናኤል፥ 9ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፥ 10ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የኤምዩድ ልጅ ኤሊሳማ፥ ከምናሴ የፈዳሱር ልጅ ገማልያል፥ 11ከብንያም የጋዲዮን ልጅ አቢዳን፥ 12ከዳን የአሚሳዲ ልጅ አክያዚር፥ 13ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋጋኤል፥ 14ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤልሳፍ፥ 15ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ። 16ከማኅበሩ የተመረጡ የእስራኤል ነገድ አለቆችና መሳፍንት በየወገናቸው እነዚህ ናቸው።” 17ሙሴና አሮንም እነዚህን በየስማቸው የተጠሩትን ሰዎች ወሰዱአቸው፤ 18በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበሩን ሁሉ ሰበሰቡአቸው፤ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ወንድ ሁሉ በየራሱ፥ በየወገኑም፥ በየአባቶቻቸውም ቤቶች፥ በየስማቸው ቍጥር ትውልዳቸውን ተናገሩ። 19እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ በሲና ምድረ በዳ ቈጠሩአቸው።
20የእስራኤል በኵር የሮቤል ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው፥ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 21ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩት አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
22የስምዖን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 23ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
24የይሁዳ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 25ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
26የይሳኮር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 27ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
28የዛብሎን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 29ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
30ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 31ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
32የምናሴ ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች- እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 33ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
34የብንያም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 35ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
36የጋድ ልጆች በየትውልዳቸው- በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 37ከጋድ ነገድ የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ።
38የዳን ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደእየ ስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 39ከዳን ነገድ የተቈጠሩት ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
40የአሴር ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 41ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
42የንፍታሌም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው፥ በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደ እየስማቸው ቍጥር፥ በየራሳቸው ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለው ወንድ ሁሉ፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 43ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
44ሙሴና አሮን ዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል አለቆች እነርሱን የቈጠሩበት ቍጥር ይህ ነው። 45ከእያንዳንዱ ነገድ ከየአባቶቻቸው ቤቶች አንድ አንድ አለቃ ነበረ። ከእስራኤልም ልጆች የተቈጠሩት ሁሉ፥ በየሠራዊታቸው፥#ዕብ. “በየአባቶቻቸው ቤቶች” ይላል። ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት፥ ወደ ሰልፍ የሚወጡት ሁሉ፥ 46የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
47ሌዋውያን ግን በየአባቶቻቸው ነገድ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም። 48እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 49“የሌዊን ነገድ እንዳትቈጥራቸው፥ ቍጥራቸውንም ከእስራኤል ልጆች ጋር እንዳትቀበል ዕወቅ፤ 50ነገር ግን በምስክሩ ድንኳንና በዕቃዎችዋ ሁሉ፥ በውስጥዋም ባለው ነገር ሁሉ ላይ ሌዋውያንን አቁማቸው። ድንኳንዋንና ዕቃዎችዋን ሁሉ ይሸከሙ፤ ያገልግሉአትም፤ በድንኳንዋም ዙሪያ ይስፈሩ። 51ድንኳንዋም ስትነሣ ሌዋውያን ይንቀሉአት፤ ድንኳንዋም ስታርፍ ሌዋውያን ይትከሉአት፤ ሌላ ሰው ግን ለመንካት ቢቀርብ ይገደል። 52የእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው በየሰፈሩ፥ እያንዳንዱም ሰው በየአለቃው፥ በየጭፍራውም ይሰፍራሉ። 53ነገር ግን በእስራኤል ልጆች ላይ ዕዳ እንዳይሆንባቸው ሌዋውያን በምስክሩ ድንኳን ዙሪያ ፊት ለፊት ይስፈሩ፤ ሌዋውያን የምስክሩን ድንኳን ሕግ ይጠብቁ።” 54የእስራኤል ልጆችም እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን ያዘዛቸውን ሁሉ አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 1: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ