መጽሐፈ ነህምያ 9
9
ሕዝቡ ኀጢአታቸውን መናዘዛቸው
1በዚህም ወር በሃያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው ተሰበሰቡ። 2የእስራኤልም ልጆች ከባዕድ ሕዝብ ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፤ ቆመውም ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኀጢአት ተናዘዙ። 3በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ#ዕብ. “የቀን ሩብ ያህል አነበቡ ሦስት የቀን ሩብ ያህልም ተናዘዙ” የሚል ይጨምራል። አነበቡ፤ ለእግዚአብሔርም ተናዘዙ፤ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ። 4ሌዋውያኑም ኢያሱና የቀድምኤል ልጆች፥ የሰራብያ ልጅ ሴኬንያ፥#ዕብ. “...ባኒ፥ ቀድምኤል፥ ሰበንያ፥ ቡኒ፥ ሰራብያ፥ ከናኒ” የሚሉ ስሞችን ይጨምራል። የከናኒ ልጆችም በደረጃዎች ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ጮኹ።
5ሌዋውያኑም ኢያሱና ቀድምኤል፥#ዕብ. “...ባኒ አሰበንያ ሰራብያ ሆዲያ ሰበንያ ፈታያ” የሚሉ ስሞችን ይጨምራል። እንዲህ አሉ፥ “ቆማችሁ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም አምላካችንን እግዚአብሔርን አመስግኑ። የከበረ ስሙንም አመስግኑ፤ በበረከትና በምስጋናም ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አድርጉት።”
የዕዝራ ጸሎት
6ዕዝራም እንዲህ አለ፥ “አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ፈጥረሃል፤ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። 7አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ፤ አብራምን መረጥህ፤ ከዑር ከላውዴዎንም አወጣኸው፤ ስሙንም አብርሃም አልኸው፤ 8ልቡም በፊትህ የታመነ ሆኖ አገኘኸው፤ የከነዓናዊውንና የኬጤዎናዊውን፥ የአሞሬዎናዊውንም፥ የፌርዜዎናዊውንም፥ የኢያቡሴዎናዊውንም፥ የጌርጌሴዎናዊውንም ምድር ለእርሱና ለዘሩ ትሰጥ ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፤ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን አጸናህ።
9“በግብጽም ሳሉ የአባቶቻችንን መከራ አየህ፤ በኤርትራ ባሕርም ሳሉ ጩኸታቸውን ሰማህ፤ 10እንደ ታበዩባቸውም ዐውቀህ ነበርና በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ፥ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትንና ተአምራትን አሳየህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስምህን አስጠራህ። 11ከፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፤ በባሕሩም መካከል በደረቅ ዐለፉ፤ የተከተሉአቸውን ግን ድንጋይ በጥልቅ ውኃ እንዲጣል በቀላይ ውስጥ ጣልሃቸው። 12የሚሄዱበትንም መንገድ ታበራላቸው ዘንድ ቀን በደመና ዐምድ፥ ሌሊትም በእሳት ዐምድ መራሃቸው። 13ወደ ሲናም ተራራ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው፤ ቅኑን ፍርድና እውነቱን ሕግ፥ መልካሙንም ሥርዐትና ትእዛዝ ሰጠሃቸው፤ 14የተቀደሰውንም ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዝንና ሥርዐትን፥ ሕግንም በባሪያህ በሙሴ እጅ አዘዝሃቸው። 15ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራን ሰጠሃቸው፤ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃን አወጣህላቸው፤ ትሰጣቸውም ዘንድ እጅህን የዘረጋህባትን ምድር ገብተው ይወርሷት ዘንድ አዘዝሃቸው።
16“ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፤ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ 17ለመስማትም እንቢ አሉ፤ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፤ ለባርነታቸውም ወደ ግብፅ ይመለሱ ዘንድ አለቃን ሾሙ፤ አንተ ግን መሓሪና ይቅር ባይ አምላክ፥ ለቍጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፤ አልተውሃቸውም። 18ዳግመኛም ቀልጦ የተሠራውን እንቦሳ አድርገው፦ ‘ከግብፅ ያወጡን አምላኮቻችን እሊህ ናቸው’ አሉ፤ እጅግም አስቈጡህ፤ 19አንተ ግን ምሕረትህ ብዙ ነውና በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድን በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዘንድ የእሳት ዓምድን በሌሊት ከእነርሱ አላራቅህም። 20ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፤ ለጥማታቸውም ውኃን ሰጠሃቸው። 21አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፤ ምንም አላሳጣሃቸውም፤ ልብሳቸውም አላረጀም፤ እግራቸውም አላበጠም።
22“መንግሥታትንና አሕዛብን ዕድል ፈንታ አድርገህ ሰጠሃቸው፤ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። 23ልጆቻቸውንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ተናገርህላቸው ምድር አገባሃቸው። 24እነርሱም ወረሱአት፤ በከነዓን ምድር የሚኖሩትንም ሰዎች በፊታቸው አጠፋሃቸው፤ የሚወድዱትንም ነገር ያደርጉባቸው ዘንድ እነርሱንና ነገሥታቶቻቸውን፥ የምድሩንም አሕዛብ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 25ምሽጎቹንም ከተሞች፥#ዕብ. “የሰባውን ምድር ወሰዱ” ይላል። መልካምን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጕድጓዶች፥ የወይኖቹንና የወይራዎቹን ቦታዎች፥ ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፤ በሉም፤ ጠገቡም፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው።
26“ነገር ግን ተመልሰው ዐመፁብህ፤ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፤ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፤ እጅግም አስቈጡህ። 27ስለዚህ በሚያሠቃዩአቸው ሰዎች እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤ አስጨነቋቸውም፤ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፤ ከሰማይም ሰማሃቸው፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው፤ ከሚያሠቃዩአቸውም እጅ አዳንሃቸው። 28ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፤ በጠላቶቻቸውም እጅ ተውሃቸው፤ ገዙአቸውም፤ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፤ 29ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፤ ነገር ግን አልሰሙህም፤ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ትእዛዝህንና ፍርድህን ተላለፉ፤ ጀርባቸውን ሰጡ፤ አንገታቸውንም አደነደኑ፤ አልሰሙምም። 30ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፤ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው፤ አላደመጡም፤ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። 31ነገር ግን አንተ ኀያል፥ ቸርና መሓሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፤ አልተውሃቸውምም።
32“አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኀያል ጽኑዕና#“ጽኑዕና” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በግእዝ ብቻ። የተፈራኸው አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ በእኛና በነገሥታቶቻችን፥ በአለቆቻችንም፥ በካህናቶቻችንም፥ በነቢያቶቻችንም፥ በአባቶቻችንም፥ በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ። 33በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም እጅግ በድለናልና። 34ነገሥታቶቻችን፥ አለቆቻችንም፥ ካህናቶቻችንም፥ አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዝህንና የመሰከርህባቸውን ምስክርህንም አልሰሙም። 35በመንግሥትህም#ዕብ. “በመንግሥታቸው” ይላል። በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠሃቸው በሰፊውና በሰባው ምድር አልተገዙልህም፤ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም። 36እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፤ ፍሬዋንና በረከቷን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥ 37ስለ ኀጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከቷን ታበዛለች፤ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፤ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፤ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን። 38ስለዚህም ሁሉ የታመነውን ቃል ኪዳን አድርገን እንጽፋለን፤ አለቆቻችንም፥ ሌዋውያኖቻችንም፥ ካህናቶቻችንም ያትሙበታል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 9: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ