መጽሐፈ ነህምያ 5
5
1በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። 2“ከወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ጋር ብዙዎች ነን፤ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት” የሚሉ ነበሩ። 3“ከራብ የተነሣም#“ከራብ የተነሣ” የሚለው በዕብ. ብቻ። እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንንና ወይናችንን፥ ቤታችንንም አስይዘናል” የሚሉ ነበሩ። 4ሌሎቹም “ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤ 5አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፤ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፤ ታላላቆችም እርሻችንንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም” የሚሉ ነበሩ።
6እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ዐዘንሁ።#ዕብ. “ተቈጣሁ” ይላል። 7በልቤም አሰብሁ፤ ታላላቆቹንና ሹሞቹንም፥ “ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ” ብዬ ተጣላኋቸው፤ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። 8እኔም፥ “ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፤ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን?” አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፤ መልስም አላገኙም። 9ደግሞም አልሁ፥ “የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? 10እኔ ደግሞ፥ ወንድሞችም፥ ብላቴኖችም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፤ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። 11እርሻቸውን፥ የወይናቸውንና የወይራቸውን ቦታ፥ ቤታቸውንም፥ ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን#ዕብ. “ከመቶ እጅ አንድ እጅ” ይላል። እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።” 12እነርሱም፥ “እንመልስላቸዋለን፤ ከእነርሱም ምንም አንሻም፤ እንደተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። 13ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፥ “ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፤ እንዲሁ የተራገፈና ባዶ ይሁን” አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፥ “አሜን” አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ።
14ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርተሰስታ ከሃያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞች ለአለቃ የሚገባውን ቀለብ አልበላንም። 15ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፤ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሰለጥኑ ነበር። እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። 16ደግሞም የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፤ እርሻም አልገዛሁም፤ ብላቴኖችም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ። 17ደግሞም በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ወደ እኛ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹሞቹ#“ከሹሞቹ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ። 18ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች፥ አንድ ፍየልም፥ በዐሥር በዐሥር ቀንም ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፤ ነገር ግን አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ከብዶ ነበርና ለአለቃ የሚገባውን ቀለብ አልሻም ነበር። 19አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ ለበጎነት አስብልኝ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ