መጽሐፈ ነህምያ 3
3
1ታላቁም ካህን ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ መቶ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት። 2በአጠገቡም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ የዘኩር ልጆች ሠሩ።
3የአስናሃ ልጆችም የዓሣ በር ሠሩ፤ ሠረገሎቹንም አኖሩ፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ። 4በአጠገባቸውም የቆስ ልጅ የኡርያ ልጅ ሚራሞት ይሠራ ጀመረ። በአጠገባቸውም የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም ይሠራ ጀመረ። በአጠገባቸውም የበሃና ልጅ ሳዶቅ ይሠራ ጀመረ። 5በአጠገባቸውም ቴቁሓውያን ይሠሩ ጀመሩ፤ ታላላቆቻቸው ግን ለሥራው አንገታቸውን አላዋረዱም።
6የፋሴሓ ልጅ ኢዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም አሮጌውን#ግእዝ “ያስናይ” ይላል አሮጌ ማለት ነው። በር አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ። 7በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መልጥያና ሜሮናታዊው ያዴን፥ እስከ ወንዙም ማዶ አለቃ ግዛት የሆኑ የገባዖንና የመሴፋ ሰዎች ሠሩ። 8በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐሬህያ ልጅ ዑዝኤል ሠራ። በአጠገቡም ከሽቱ ቀማሚዎች የነበረ ሐናንያ ሠራ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን ጠገኑ። 9በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ አለቃ የሆር ልጅ ረፋያ ሠራ። 10በአጠገባቸውም የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን ሠራ። በአጠገቡም የአሰብንብሔም ልጅ ሐጡስ ሠራ። 11የካሪም ልጅ መልክያ፥ የፈሐት ሞዓብ ልጅም አሱብ ሌላውን ክፍልና#“ሌላውን ክፍልና” የሚለው በዕብ. ብቻ። የእቶኑን ግንብ ሠሩ። 12በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኩሌታ ገዢ የአሎኤስ ልጅ ሰሎምና ሴቶች ልጆቹ ሠሩ።
13ሐኖንና የዘናን ሰዎችም የሸለቆውን በር አደሱ፤ ሠሩት፤ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ፤ ደግሞም እስከ ጕድፍ መጣያ በር ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ።
14የቤትሐካሪምም ግዛት ገዢ የሬካብ ልጅ መልክያ ከወንድሞቹና ከልጆቹ ጋር#“ከወንድሞቹና ከልጆቹ ጋር” የሚለው በዕብ. የለም። የጕድፍ መጣያውን በር ሠራ፤ ከደነው፤ ሳንቃዎቹንም አቆመ፤ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ።
15የመሴፋም ገዢ የኮልሐዜ ልጅ ሰሎም የምንጩን በር አደሰ፤ ሠራው፤ ከደነውም፤ ሳንቃዎቹንም አቆመ፤ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ከዳዊትም ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ያለውን የመዋኛ ቅጥር ሠራ። 16ከእርሱም በኋላ የቤሶር ግዛት እኩሌታ ገዢ የዓዛቡህ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር አንጻር እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራውም መዋኛ፥ እስከ ኀያላኑም ቤት ድረስ ሠራ። 17ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሁም ሠሩ። በአጠገባቸውም የቅዒላ ግዛት እኩሌታና የአውራጃዎችዋ ገዢ አሰብያ ሠራ። 18ከእርሱም በኋላ የቅዔላ ግዛት እኩሌታ ገዢ የኤንሐዳድ ልጅ ቤኒይና ወንድሞቹ ሠሩ። 19በአጠገቡም የመሴፋ ገዢ የኢያሱ ልጅ አዙር በማዕዘኑ አጠገብ በመወጣጫው ግንብ አንጻር ያለውን ሌላውን ክፍል ሠራ። 20ከእርሱም በኋላ የዘቡር ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል ተግቶ ሠራ። 21ከእርሱም በኋላ የአቆስ ልጅ የኡርያ ልጅ ሚራሞት ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እሰከ ኤልያሴብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል ሠራ። 22ከእርሱም በኋላ የአካባቢው ሰዎች ካህናቱ ሠሩ። 23ከእነርሱም በኋላ ብንያምና አሴብ በቤታቸው አንጻር ያለውን ሠሩ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዓስያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን ሠራ። 24ከእርሱም በኋላ የኢንሓዳድ ልጅ ባኒ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ እስከ ግንቡመዞሪያ ድረስ ያለውን ሌላውን ክፍል ሠራ። 25የኡዛይ ልጅ ፋልል በማዕዘኑ አንጻር ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ሠራ። 26ናታኒምም በዖፌል በውኃው በር አንጻር በምሥራቅ በኩል ወጥቶ በቆመው ግንብ አጠገብ እስካለው ስፍራ ድረስ ተቀመጡ። 27ከእርሱም በኋላ ቴቁሐውያን ወጥቶ በቆመው በታላቁ ግንብ አንጻር ያለውን እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሌላውን ክፍል ሠሩ።
28ከፈረሶች በር በላይ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየቤታቸው አንጻር ሠሩ። 29ከዚያም በኋላ የሄሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ አንጻር ያለውን ሠራ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቁ በር ጠባቂ የሴኬንያ ልጅ ሰማያ ሠራ። 30ከእርሱም በኋላ የሰሎምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኖን ሌላውን ክፍል ሠሩ። ከዚያም በኋላ የበራክያ ልጅ ሜሱላም በሙዳየ ምጽዋቱ አንጻር ያለውን ሠራ። 31ከእርሱም በኋላ የሰራፊ ልጅ#ዕብ. “ከወርቅ አንጥረኞች የነበረ” ይላል። መልክያ እስከ ናታኒምና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት ድረስ በሐሜፍቃድ በር አንጻር ያለውን እስከ ማዕዘኑ መውጫ ድረስ ሠራ። 32ከማዕዘኑም መውጫ ጀምረው እስከ በጎች በር ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች ሠሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነህምያ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ