የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 3

3
ኢየሱስ እጀ ሽባውን ሰው እንደፈወሰ
(ማቴ. 12፥9-14ሉቃ. 6፥6-11)
1ደግሞም ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር፤ 2ሊከሱትም በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። 3እጁ የሰለለችውንም ሰው “ተነሥተህ ወደ መካከል ና፤” አለው። 4“በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል?” አላቸው፤ እነርሱም ዝም አሉ። 5ስለ ልባቸውም ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸው፤ ሰውየውንም “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። ዘረጋትም፤ እጁም ዳነች። 6ፈሪሳውያንም ወጥተው ወዲያው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ከሄሮድስ ወገን ጋር ተማከሩበት።
ሕዝቡ በባሕሩ አጠገብ እንደተሰበቡ
7ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ 8እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገ ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። 9ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ 10ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። 11ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” እያሉ ጮኹ። 12እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው።
ስለ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መመረጥ
(ማቴ. 10፥1-4ሉቃ. 6፥14-16)
13ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ። 14ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ 15ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለት አደረገ፤ 16ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ 17የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፤ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ 18እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ 19አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን።
የጸሐፍት ከንቱ ወሬ
(ማቴ. 12፥22-32ሉቃ. 11፥14-2312፥10)
20ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። 21ዘመዶቹም ሰምተው “አበደ” ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። 22ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም “ብዔል ዜቡል አለበት፤” ደግሞ “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል፤” ብለው ተናገሩ። 23እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው “ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? 24መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ 25ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። 26ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። 27ነገር ግን አስቀድሞ ኀይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም፤ ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።
28“እውነት እላችኋለሁ፤ ለሰው ልጆች ኀጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ 29በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።” 30“ርኵስ መንፈስ አለበት፤” ይሉ ነበርና።
ስለ ኢየሱስ እናት እና ወንድሞቹ
(ማቴ. 12፥46-50ሉቃ. 8፥19-21)
31እናቱና ወንድሞቹም መጡ፤ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። 32ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና “እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል፤” አሉት። 33መልሶም “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው?” አላቸው። 34በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና “እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። 35የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው፤ እኅቴም፤ እናቴም፤” አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 3