የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 2

2
ኢየሱስ አንድ ሽባ ሰው እንደፈወሰ
(ማቴ. 9፥1-8ሉቃ. 5፥17-26)
1ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ደግሞ ገብቶ በቤት እንደ ሆነ ተሰማ። 2በደጅ ያለው ስፍራም እስኪጠባቸው ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ይነግራቸው ነበር። 3አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። 4ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፤ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። 5ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “አንተ ልጅ! ኀጢአትህ ተሰረየችልህ፤” አለው። 6ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም “ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? 7ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል፤” ብለው አሰቡ። 8ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው “በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ? 9ሽባውን ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ፤’ ከማለት ወይስ ‘ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ፤’ ከማለት ማናቸው ይቀላል? 10ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” 11ሽባውን “አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። 12ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፤ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና “እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም፤” ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ።
የሌዊ መጠራት
(ማቴ. 9፥9-13ሉቃ. 5፥27-32)
13ደግሞም በባሕር አጠገብ ወጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። 14ሲያልፍም በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አየና “ተከተለኝ፤” አለው። ተነሥቶም ተከተለው።
15በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ ብዙ ቀራጮችና ኀጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጡ፤ ብዙ ነበሩ፤ ይከተሉትም ነበር። 16ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ “ከቀራ ጮችና ከኀጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው?” አሉ። 17ኢየሱስም ሰምቶ “ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም፤” አላቸው።
ስለጾም የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 9፥14-17ሉቃ. 5፥33-39)
18የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር። መጥተውም “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት የሚጾሙት የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ስለ ምንድር ነው?” አሉት። 19ኢየሱስም አላቸው “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊጾሙ አይችሉም። 20ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ወራትም ይጾማሉ። 21በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ መጣፊያ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። 22በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳል፤ የወይኑም ጠጅ ይፈሳል፤ አቁማዳውም ይጠፋል፤ አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ያኖራሉ።”
ስለ ሰንበት የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 12፥1-8ሉቃ. 6፥1-5)
23በሰንበትም በእርሻ መካከል ሲያልፍ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። 24ፈሪሳውያንም “እነሆ፥ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለ ምን ያደርጋሉ?” አሉት። 25እርሱም “ዳዊት ባስፈለገውና በተራበ ጊዜ፥ እርሱ አብረውት ከነበሩት ጋር ያደረገውን፥ 26አብያተር ሊቀ ካህናት በነበረ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ፥ ከካህናት በቀር መብላት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕትን እንጀራ እንደ በላ፥ ከእርሱም ጋር ለነበሩት እንደ ሰጣቸው ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። 27ደግሞ “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ 28እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው፤” አላቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 2