የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 9:1-19

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 9:1-19 አማ2000

በታንኳም ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ። እነሆም፥ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “አንተ ልጅ! አይዞህ፤ ኀጢአትህ ተሰረየችልህ፤” አለው። እነሆም ከጻፎቹ አንዳንዶቹ በልባቸው “ይህስ ይሳደባል፤” አሉ። ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ “ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ’ ከማለት ወይስ ‘ተነሣና ሂድ’ ከማለት ማናቸው ይቀላል? ነገር ግን በምድር ላይ ኀጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” በዚያን ጊዜ ሽባውን “ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፤ ለሰውም እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና “ተከተለኝ” አለው። ተነሥቶም ተከተለው። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኀጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል?” አሉአቸው። ኢየሱስም ሰምቶ “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤነኞች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን ሄዳችሁ ‘ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም፤’ ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኀጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና፤” አላቸው። በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ። በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈሳል፤ አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፤ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።” ይህንም ሲነግራቸው አንድ መኰንን መጥቶ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች፤” እያለ ሰገደለት። ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች