የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 12

12
ስለ ሰንበት የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 2፥23-28ሉቃ. 6፥1-5)
1በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። 2ፈሪሳውያንም አይተው “እነሆ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ፤” አሉት። 3-4እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? 5ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኀጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን? 6ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። 7‘ምሕረትን እወዳለሁ፤ መሥዋዕትንም አይደለም፤’ ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኀጢአት የሌለባቸውን ባልኵኦነናችሁም ነበር። 8የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።”
ኢየሱስ እጀ ሽባውን እንደ አዳነ
(ማር. 3፥1-6ሉቃ. 6፥6-11)
9ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ። 10እነሆም እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ “በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን?” ብለው ጠየቁት። 11እርሱ ግን “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? 12እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል፤” አላቸው። 13ከዚያም በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ፤” አለው። ዘረጋትም፤ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። 14ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።
15ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሁሉንም ፈወሳቸው፤ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ 16-17በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል
18“እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥
ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤
መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤
ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል።
19አይከራከርም፤ አይጮህምም፤
ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም።
20ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥
የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤
የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም።
21አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”
ኢየሱስ ጋኔን ያደረበትን ዕውርና ድዳ ሰው እንደፈወሰ
(ማር. 3፥20-30ሉቃ. 11፥14-23)
22ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ድዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው። 23ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና “እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን?” አሉ። 24ፈሪሳውያን ግን ሰምተው “ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም፤” አሉ። 25ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤” እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። 26ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፤ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? 27እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። 28እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። 29ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። 30ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። 31ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም። 32በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።
33“ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፤ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። 34እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። 35መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። 36እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ 37ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ።”
ተአምራት ለማየት የቀረበ ጥያቄ
(ማር. 8፥11-12ሉቃ. 11፥29-32)
38በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና “መምህር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን፤” አሉ። 39እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። 40ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል። 41የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። 42ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።
ስለ ርኩሳን መናፍስት
(ሉቃ. 11፥24-26)
43“ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውሃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ አያገኝምም። 44በዚያን ጊዜም ‘ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል። 45ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፤ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።”
46ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። 47አንዱም “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል፤” አለው። 48እርሱ ግን ለነገረው መልሶ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አለው። 49እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ “እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤ 50በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና፤” አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 12