የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 11

11
ከመጥምቁ ዮሐንስ የተላኩ መልእክተኞች
(ሉቃ. 7፥17-35)
1ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ።
2ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና 3“የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” አለው። 4ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ ንገሩት፤ 5ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ 6ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው።”
7እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? 8ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። 9ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን።
10‘እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ
መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤’
11ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 12ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል። 13ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ 14ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። 15የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
16ነገር ግን “ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፤ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ 17‘እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ፤ ዋይ ዋይም አላላችሁም’ ይሉአቸዋል። 18ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘ጋኔን አለበት’ አሉት። 19የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች።”
ንስሓ ባለመግባታቸው የተወቀሱ ከተሞች
(ሉቃ. 10፥13-15)
20በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ 21“ወዮልሽ ኮራዚ! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። 22ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 23አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። 24ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል።”
25በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “አባት ሆይ! የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። 26አዎን አባት ሆይ! ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። 27ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። 28እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። 29ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ 30ቀንበሬ ልዝብ፤ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 11