ጌታችን ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተመልሶ ወደ ገሊላ ሄደ፤ ዝናውም በሀገሩ ሁሉ ተሰማ። በየምኵራባቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር። ወደ አደገበት ወደ ናዝሬትም ሄደ፤ በሰንበት ቀንም እንዳስለመደ ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩን የኢሳይያስንም መጽሐፍ ሰጡት፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ እንዲህ የሚል የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። “የእግዚአብሔር መንፈስ በላዬ ነው፤ ስለዚህ ቀብቶ ለድሆች የምሥራችን እነግራቸው ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፥ ያዘኑትንም ደስ አሰኛቸው ዘንድ፥ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፥ የተገፉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የታሰሩትንም እፈታቸው ዘንድ፥ የቈሰሉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ላከኝ።” መጽሐፉንም አጥፎ ለተላላኪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራብም የነበሩት ሁሉ ዐይናቸውን አትኲረው ተመለከቱት። እርሱም፥ “የዚህ የመጽሐፍ ነገር ዛሬ በጆሮአችሁ ደረሰ፤ ተፈጸመም” ይላቸው ጀመር። ሁሉም የንግግሩን መከናወን መሰከሩለት፤ የአንደበቱንም ቅልጥፍና እያደነቁ፥ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር። እርሱም፥ “በውኑ ባለ መድኀኒት ራስህን አድን፤ በቅፍርናሆም ያደረግኸውንና የሰማነውን ሁሉ በዚህም በሀገርህ ደግሞ አድርግ ብላችሁ ይህችን ምሳሌ ትመስሉብኛላችሁ” አላቸው። እንዲህም አላቸው፥ “እውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በሀገሩ አይከብርም። እውነት እላችኋለሁ፤ በነቢዩ በኤልያስ ዘመን በምድር ሁሉ ብርቱ ረኃብ እስኪሆን ድረስ ሰማይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር በተዘጋበት ጊዜ ብዙ መበለቶች በእስራኤል ውስጥ ነበሩ። ኤልያስ የሲዶና ክፍል በምትሆን በስራጵታ ወደምትኖር ወደ አንዲት መበለት ሴት እንጂ ከእነዚህ ወደ አንዲቱ እንኳን አልተላከም። በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም ብዙ ለምጻሞች በእስራኤል ውስጥ ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነዚያ አንድ እንኳን አልነጻም።” በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ይህን ሰምተው ተቈጡ። ያንጊዜም ተነሥተው ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፤ ገፍተውም ይጥሉት ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ተራራ ጫፍ ወሰዱት። እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
የሉቃስ ወንጌል 4 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 4:14-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos