የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 4:14-30

የሉቃስ ወንጌል 4:14-30 አማ05

ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተሞልቶ ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አካባቢዎች ሁሉ ተሰማ። በምኲራቦቻቸውም ያስተምር ነበር፤ ሁሉም በትምህርቱ አመሰገኑት። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ አደገበት አገር ወደ ናዝሬት ሄደ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኲራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ፤ የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ተሰጠው፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፤ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ መልካም ዜናን ለድኾች እንዳበሥር ሾሞኛል፤ ለታሰሩት መፈታትን፥ ለዕውሮች ማየትን እንዳውጅና የተጨቈኑትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል፤ እንዲሁም ጌታ ሕዝቡን የሚያድንበትን የጸጋ ዓመት እንዳስታውቅ ልኮኛል።” ኢየሱስ መጽሐፉን አጥፎ ለአስተናባሪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራቡ የነበሩትም ሁሉ ትኲር ብለው ወደ እርሱ ይመለከቱ ጀመር፤ እርሱም “እነሆ! ይህ አሁን ሲነበብ የሰማችሁት የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” አላቸው። ስለ እርሱ ሁሉም መልካም ይናገሩ ነበር፤ በሚናገረውም ጸጋን የተመላ ቃል ተደንቀው “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ ‘አንተ ሐኪም፥ እስቲ ራስህን አድን፥’ የሚለውን ምሳሌ እንደምትጠቅሱብኝ እርግጠኛ ነኝ፤ እንዲሁም ‘በቅፍርናሆም አድርገሃል ሲሉ የሰማነውን ሁሉ፥ እዚህም በገዛ አገርህ አድርግ’ ትሉኛላችሁ። በእውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ ሰዎች ዘንድ አይከበርም። “ስሙኝ እውነቱን ልንገራችሁ፤ በነቢዩ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናም ባለመዝነቡ በአገሩ ሁሉ ብርቱ ራብ ሆኖ ነበር፤ በዚያን ጊዜ በእስራኤል አገር ብዙ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ነበሩ። ነገር ግን ኤልያስ፥ በሲዶና አገር ሰራጵታ በምትባል መንደር ወደምትገኘው ወደ አንዲት ባልዋ የሞተባት ሴት ብቻ ተላከ እንጂ ወደ ሌላ ወደ ማንም አልተላከም። እንዲሁም በነቢዩ በኤልሳዕ ጊዜ ብዙ ለምጻሞች በእስራኤል አገር ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ አልነጻም።” በምኲራብ የነበሩትም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። ተነሥተውም ኢየሱስን ጐትተው ከከተማ ውጪ አወጡት፤ ወደ ገደልም ገፍትረው ሊጥሉት ፈልገው ከተማቸው ወደ ተሠራችበት ኰረብታ አፋፍ ላይ ወሰዱት። እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።