ወጥቶም እንዳስለመደው ይጸልይ ዘንድ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ከዚያም ደርሶ፥ “ወደ መከራ እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። የድንጋይ ውርወራ ያህልም ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ እየሰገደ ጸለየ። እንዲህም አለ፥ “አባት ሆይ፥ ብትፈቅድስ ይህን ጽዋ ከእኔ አሳልፈው፤ ነገር ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” የሚያበረታታው የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ታየው። ፈራ፤ መላልሶም ጸለየ፤ ላቡም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ሆነ። ከሚጸልይበትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደ፤ ከኀዘንም የተነሣ ተኝተው አገኛቸው። “ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ” አላቸው። ይህንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ ይሁዳም ይመራቸው ነበር፤ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸውም ምልክት ይህ ነበር፤ “የምስመው እርሱ ነውና እርሱን አጽንታችሁ ያዙት” አላቸው። ጌታችን ኢየሱስም ይሁዳን፥ “በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?” አለው። አብረውት የነበሩትም የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ጌታችን ኢየሱስን፥ “አቤቱ፥ በሰይፍ ልንመታቸው ትፈቅዳለህን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መታው፤ ቀኝ ጆሮውንም ቈረጠው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህንስ ተው” አለ፤ ወዲያውም ጆሮውን ዳስሶ አዳነው። ጌታችን ኢየሱስም ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን የካህናት አለቆችን፥ የቤተ መቅደስ ሹሞችንና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፥ “ሌባን እንደምትይዙ በሰይፍና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን? ዘወትርም ከእናንተ ጋር በቤተ መቅደስ ስኖር እጃችሁን እንኳ አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ጊዜያችሁ ይህ ነው፤ የጨለማው አበጋዝም ሥልጣኑ ይህ ነው።” ይዘውም ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት ወሰዱት፤ ጴጥሮስም ከሩቅ ይከተለው ነበር። በግቢውም ውስጥ እሳት አንድደው ተቀመጡ፤ ጴጥሮስም አብሮአቸው በመካከላቸው ተቀመጠ። በእሳቱም ብርሃን በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ብላቴና አየችው፤ እርሱ መሆኑንም ለየችውና፥ “ይህም ከእርሱ ጋር ነበር” አለች። እርሱ ግን፥ “ሴትዮ! የምትዪውን አላውቅም” ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አየውና፥ “አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ” አለው፤ ጴጥሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! እኔ አይደለሁም” አለው። አንዲት ሰዓት ያህልም ቈይቶ አንድ ሌላ ሰው፥ “ይህም በእውነት ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ሰውየውም የገሊላ ሰው ነው” ብሎ አስጨነቀው። ጴጥሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም” አለው፤ እርሱም ይህን ሲናገር ያንጊዜ ዶሮ ጮኸ። ጌታችን ኢየሱስም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን አየው፤ ጴጥሮስም፥ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለውን የጌታችንን ቃል ዐሰበ። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶን አለቀሰ። ጌታችን ኢየሱስን ይዘውት የነበሩት ሰዎችም ይዘባበቱበትና ይደበድቡት ነበር። ሸፍነውም ፊቱን በጥፊ ይመቱት ነበር፤ “ፊትህን በጥፊ የመታህ ማነው? ንገረን” እያሉም ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። በነጋም ጊዜ፥ የካህናት አለቆች፥ ጻፎችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱት። “አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ በግልጥ ንገረን” አሉት፤ እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ብነግራችሁም አታምኑኝም። ብጠይቃችሁም አትመልሱልኝም፤ ወይም አትተዉኝም። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።” ሁሉም፥ “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት፤ እርሱም፥ “እኔ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ” አላቸው። እነርሱም፥ “ስለ እርሱ ምን ምስክር እንሻለን? እኛ ራሳችን ሲናገር ሰምተናል” አሉ።
የሉቃስ ወንጌል 22 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 22
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 22:39-71
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos