ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ዐለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ። ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ እዘንልን” አሉ። ባያቸውም ጊዜ፥ “ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ” አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ነጻ ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ። በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና አመሰገነው፤ ሰውየውም ሳምራዊ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ? ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?” እርሱንም፥ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው። ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ጠየቁት፤ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም። እንኋት፥ በዚህ ናት፤ ወይም እነኋት፥ በዚያ ናት አይሉአትም፤ የእግዚአብሔር መንግሥትስ እነኋት፥ በመካከላችሁ ናት።” ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፥ “ከሰው ልጆች ቀኖች አንዲቱን ታዩ ዘንድ የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩአትም። እነሆ፥ በዚህ ነው፥ ወይም እነሆ፥ በዚያ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ ብልጭ ብሎ ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ እንደሚያበራ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ነውና። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ብዙ መከራን ይቀበላል፤ ይህች ትውልድም ትንቀዋለች፤ ትፈታተነዋለችም። በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡ ነበረ፤ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን አንድ አድርጎ አጠፋ። በሎጥ ዘመንም ሲበሉና ሲጠጡ፥ ቤት ሲሠሩና ተክል ሲተክሉ፥ ሲሸጡና ሲገዙ ነበረ። ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነመ፤ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ አይታወቅምም። ያንጊዜም በሰገነት ላይ ያለ፥ ገንዘቡም በምድር ቤት የሆነበት ሰው ለመውሰድ አይውረድ፤ በዱር ያለም ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት ዐስቡአት። ነፍሱን ሊያድናት የሚወድ ይጣላት፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚጥላትም ያድናታል። እላችኋለሁ፦ ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ። ሁለት ሴቶችም በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዪቱንም ይተዋሉ። ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ላይ ይኖራሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ።” እነርሱም መልሰው፥ “አቤቱ፥ ወዴት ነው?” አሉት፤ እርሱም፥ “ገደላ በአለበት አሞሮች በዚያ ይሰበሰባሉ” አላቸው።
የሉቃስ ወንጌል 17 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 17
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 17:11-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች