ሉቃስ 17:11-37
ሉቃስ 17:11-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ዐለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ። ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ እዘንልን” አሉ። ባያቸውም ጊዜ፥ “ወደ ካህን ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ” አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ነጻ ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ። በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ እግር በታች ሰገደና አመሰገነው፤ ሰውየውም ሳምራዊ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ? ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?” እርሱንም፥ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ” አለው። ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ጠየቁት፤ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም። እንኋት፥ በዚህ ናት፤ ወይም እነኋት፥ በዚያ ናት አይሉአትም፤ የእግዚአብሔር መንግሥትስ እነኋት፥ በመካከላችሁ ናት።” ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፥ “ከሰው ልጆች ቀኖች አንዲቱን ታዩ ዘንድ የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩአትም። እነሆ፥ በዚህ ነው፥ ወይም እነሆ፥ በዚያ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ ብልጭ ብሎ ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ እንደሚያበራ የሰው ልጅ አመጣጡ እንዲሁ ነውና። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ብዙ መከራን ይቀበላል፤ ይህች ትውልድም ትንቀዋለች፤ ትፈታተነዋለችም። በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡ ነበረ፤ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን አንድ አድርጎ አጠፋ። በሎጥ ዘመንም ሲበሉና ሲጠጡ፥ ቤት ሲሠሩና ተክል ሲተክሉ፥ ሲሸጡና ሲገዙ ነበረ። ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነመ፤ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ አይታወቅምም። ያንጊዜም በሰገነት ላይ ያለ፥ ገንዘቡም በምድር ቤት የሆነበት ሰው ለመውሰድ አይውረድ፤ በዱር ያለም ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት ዐስቡአት። ነፍሱን ሊያድናት የሚወድ ይጣላት፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚጥላትም ያድናታል። እላችኋለሁ፦ ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ። ሁለት ሴቶችም በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛዪቱንም ይተዋሉ። ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ላይ ይኖራሉ፤ አንዱን ይወስዳሉ፤ ሁለተኛውንም ይተዋሉ።” እነርሱም መልሰው፥ “አቤቱ፥ ወዴት ነው?” አሉት፤ እርሱም፥ “ገደላ በአለበት አሞሮች በዚያ ይሰበሰባሉ” አላቸው።
ሉቃስ 17:11-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ፣ በሰማርያና በገሊላ ድንበር በኩል ዐለፈ፤ ወደ አንድ መንደር እንደ ገባም ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት፤ እነርሱም በርቀት ቆመው፣ በታላቅ ድምፅ፣ “ኢየሱስ፤ ጌታ ሆይ፤ ራራልን!” አሉት። እርሱም ባያቸው ጊዜ፣ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው። እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ መፈወሱን ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፤ በኢየሱስም እግር ላይ በፊቱ ተደፍቶ አመሰገነው፤ ይህም ሰው ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “የነጹት ዐሥር ሰዎች አልነበሩምን? ታዲያ፣ ዘጠኙ የት ደረሱ? ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር ተመልሰው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ የሉም ማለት ነውን?” ሰውየውንም፣ “ተነሥተህ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም፤ ሰዎችም፣ ‘እዚህ ነው’ ወይም ‘እዚያ ነው’ ማለት አይችሉም፤ እነሆ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና።” ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አላቸው፤ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ደግሞም አታዩትም። ሰዎች፣ ‘እዚያ ነው’ ወይም ‘እዚህ ነው’ ይሏችኋል፤ ተከትላችኋቸውም አትሂዱ፤ ምክንያቱም መብረቅ በርቆ ሰማዩን ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅም በሚመጣበት ቀን ልክ እንደዚሁ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት የሰው ልጅ ብዙ መሠቃየትና በዚህም ትውልድ መናቅ ይኖርበታል። “በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው። “በሎጥ ዘመንም እንዲሁ ነበር፤ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ዕለት ግን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው። “የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል። በዚያ ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ፣ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱ። ነፍሱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ነፍሱን የሚያጠፋት ግን ያቈያታል። እላችኋለሁ፤ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ይተኛሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል። ሁለት ሴቶች ዐብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች [ሁለት ሰዎች በዕርሻ ቦታ ዐብረው ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”] እነርሱም መልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወሰዱት ወዴት ነው?” አሉት። እርሱም፣ “በድን ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።
ሉቃስ 17:11-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ፦ ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። አይቶም፦ ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። እርሱንም፦ ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ልታዩ የምትመኙበት ወራት ይመጣል አታዩትምም። እነርሱም፦ እነሆ በዚህ፥ ወይም፦ እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል። አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስቡአት። ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል። እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች። ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። መልሰውም፦ ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው? አሉት። እርሱም፦ ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ አላቸው።
ሉቃስ 17:11-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ያልፍ ነበር፤ ወደ አንዲት መንደርም በገባ ጊዜ ዐሥር ለምጻሞች ወደ እርሱ መጥተው በሩቅ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢየሱስ ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ኢየሱስም አያቸውና “ሂዱ! ሰውነታችሁን ለካህናት አሳዩ!” አላቸው፤ እነርሱም በመሄድ ላይ ሳሉ ከለምጻቸው ነጹ። ከእነርሱም አንዱ ከለምጹ መንጻቱን ባየ ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ተመለሰ። ኢየሱስንም እያመሰገነ በእግሩ ሥር በግምባሩ ተደፋ፤ እርሱ የሰማርያ ሰው ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከለምጽ የነጹት ሰዎች ዐሥር አልነበሩምን? ታዲያ፥ ዘጠኙ የት አሉ? እግዚአብሔርን ለማመስገን ተመልሶ የመጣ ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር ሌላ አንድም አልተገኘምን?” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው፦ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ፈሪሳውያን ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ሲሉ ጠየቁት፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ሰዎች ነቅተው በሚጠባበቁት ዐይነት አይደለም፤ እንዲሁም ‘እነሆ፥ እዚህ ናት ወይም እዚያ ናት’ የምትባል አይደለችም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ነች።” ቀጥሎም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትናፍቁበት ቀን ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩም። ሰዎች ‘እነሆ፥ ክርስቶስ እዚህ ነው! ወይም እዚያ ነው!’ ይሉአችኋል፤ ነገር ግን አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በሰማይ ላይ ሲበርቅ ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ የሰው ልጅ በሚመጣበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አስቀድሞ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህ ትውልድም ሊናቅና ሊነቀፍ ግድ ነው። በኖኅ ዘመን እንደሆነው ዐይነት የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡም ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጥፋት ውሃ መጣና አጥለቅልቆ ሁሉንም አጠፋቸው። እንዲሁም ደግሞ በሎጥ ዘመን እንደሆነው ዐይነት ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲሸጡና ሲገዙ፥ አትክልት ሲተክሉና ቤትም ሲሠሩ ነበር። ነገር ግን ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋቸው፤ የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀንም እንዲሁ ይሆናል። “በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመውሰድ አይውረድ፤ በእርሻም ቦታ ያለ ሰው ወደ ቤቱ አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱ! ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ያድናታል። በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ ከእነርሱም አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል እላችኋለሁ። ሁለት ሴቶች በአንድ ቦታ አብረው ይፈጫሉ፤ አንድዋ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች። [ ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ቦታ ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”] ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው የሚወሰዱት” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “በድን ባለበት አሞራዎች ይሰበሰባሉ” ሲል መለሰላቸው።
ሉቃስ 17:11-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ “ኢየሱስ ሆይ! መምህር ሆይ! ማረን፤” አሉ። አይቶም “ሂዱ፤ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ፤” አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያወደሰ ተመለሰ፤ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ “ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከሌላ ወገን ሰው በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም፤” አለ። እርሱንም “ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፤” አለው። ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ደግሞም ‘ይችትና!’ ወይም ‘ያቻትና!’ የምትባል አይደለችም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና፤” አላቸው። ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች መካከል አንዱን ለማየት የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ አታዩትምም። እነርሱም ‘እነሆ በዚህ’ ወይም ‘እነሆ በዚያ’ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ አንድ ስፍራ ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ ስፍራ እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅም፥ በቀኑ፥ እንዲህ ይሆናል። አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህም ትውልድ ሊናቅ ይገባዋል። በኖኅ ዘመንም እንደሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመንም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፤ የጥፋት ውሃም መጣ፤ ሁሉንም አጠፋ። እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ፤ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፤ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱአት። ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን የሚያጠፋ ሁሉ ይጠብቃታል። በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሁለተኛውም ይቀራል እላችኋለሁ። ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች፤ ሁለተኛይቱም ትቀራለች። ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሁለተኛውም ይቀራል።” ሲመልሱለትም “ጌታ ሆይ! ወዴት ነው?” አሉት። እርሱም “ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ፤” አላቸው።