የሉቃስ ወንጌል 17:11-37

የሉቃስ ወንጌል 17:11-37 አማ05

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ያልፍ ነበር፤ ወደ አንዲት መንደርም በገባ ጊዜ ዐሥር ለምጻሞች ወደ እርሱ መጥተው በሩቅ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢየሱስ ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ኢየሱስም አያቸውና “ሂዱ! ሰውነታችሁን ለካህናት አሳዩ!” አላቸው፤ እነርሱም በመሄድ ላይ ሳሉ ከለምጻቸው ነጹ። ከእነርሱም አንዱ ከለምጹ መንጻቱን ባየ ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ተመለሰ። ኢየሱስንም እያመሰገነ በእግሩ ሥር በግምባሩ ተደፋ፤ እርሱ የሰማርያ ሰው ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከለምጽ የነጹት ሰዎች ዐሥር አልነበሩምን? ታዲያ፥ ዘጠኙ የት አሉ? እግዚአብሔርን ለማመስገን ተመልሶ የመጣ ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር ሌላ አንድም አልተገኘምን?” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው፦ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው። ፈሪሳውያን ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ሲሉ ጠየቁት፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ሰዎች ነቅተው በሚጠባበቁት ዐይነት አይደለም፤ እንዲሁም ‘እነሆ፥ እዚህ ናት ወይም እዚያ ናት’ የምትባል አይደለችም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ነች።” ቀጥሎም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትናፍቁበት ቀን ይመጣል፤ ነገር ግን አታዩም። ሰዎች ‘እነሆ፥ ክርስቶስ እዚህ ነው! ወይም እዚያ ነው!’ ይሉአችኋል፤ ነገር ግን አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። መብረቅ በሰማይ ላይ ሲበርቅ ከዳር እስከ ዳር እንደሚያበራ የሰው ልጅ በሚመጣበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አስቀድሞ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህ ትውልድም ሊናቅና ሊነቀፍ ግድ ነው። በኖኅ ዘመን እንደሆነው ዐይነት የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያገቡና ሲጋቡም ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጥፋት ውሃ መጣና አጥለቅልቆ ሁሉንም አጠፋቸው። እንዲሁም ደግሞ በሎጥ ዘመን እንደሆነው ዐይነት ይሆናል፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲሸጡና ሲገዙ፥ አትክልት ሲተክሉና ቤትም ሲሠሩ ነበር። ነገር ግን ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋቸው፤ የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀንም እንዲሁ ይሆናል። “በዚያን ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመውሰድ አይውረድ፤ በእርሻም ቦታ ያለ ሰው ወደ ቤቱ አይመለስ። የሎጥን ሚስት አስታውሱ! ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሁሉ ያድናታል። በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይተኛሉ፤ ከእነርሱም አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል እላችኋለሁ። ሁለት ሴቶች በአንድ ቦታ አብረው ይፈጫሉ፤ አንድዋ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች። [ ሁለት ሰዎች በአንድ እርሻ ቦታ ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”] ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው የሚወሰዱት” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “በድን ባለበት አሞራዎች ይሰበሰባሉ” ሲል መለሰላቸው።