የሉ​ቃስ ወን​ጌል 11:1-13

የሉ​ቃስ ወን​ጌል 11:1-13 አማ2000

ከዚ​ህም በኋላ በአ​ን​ዲት ቦታ ጸለየ፤ ጸሎ​ቱን በጨ​ረሰ ጊዜም ከደቀ መዛ​ሙ​ርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ፥ ዮሐ​ንስ ለደቀ መዛ​ሙ​ርቱ እንደ አስ​ተ​ማ​ራ​ቸው ጸሎት አስ​ተ​ም​ረን” አለው። እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “በም​ት​ጸ​ል​ዩ​በት ጊዜ እን​ዲህ በሉ፦ በሰ​ማ​ያት የም​ት​ኖር አባ​ታ​ችን ሆይ፥ ስምህ ይቀ​ደስ፤ መን​ግ​ሥ​ትህ ትምጣ፤ ፈቃ​ድህ በሰ​ማይ እንደ ሆነ እን​ዲ​ሁም በም​ድር ይሁን። የዕ​ለት ምግ​ባ​ች​ንን በየ​ዕ​ለቱ ስጠን። እኛም የበ​ደ​ለ​ንን ሁሉ ይቅር እን​ድ​ንል በደ​ላ​ች​ንን ይቅር በለን፤ አቤቱ፥ ወደ ፈተና አታ​ግ​ባን፤ ከክፉ ሁሉ አድ​ነን እንጂ።” እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ከመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ ወዳጅ ያለው ሰው ቢኖር በመ​ን​ፈቀ ሌሊ​ትም ወደ እርሱ ሄዶ እን​ዲህ ቢለው፦ ‘ወዳጄ ሆይ ሦስት እን​ጀራ አበ​ድ​ረኝ። ወዳጄ ከመ​ን​ገድ መጥ​ቶ​ብ​ኛ​ልና የማ​ቀ​ር​ብ​ለት የለ​ኝም።’ ያ ወዳ​ጁም ከው​ስጥ ሆኖ፦ ‘አት​ዘ​ብ​ዝ​በኝ፤ ደጁን አጥ​ብ​ቀን ዘግ​ተ​ናል፤ ልጆ​ችም ከእኔ ጋር በአ​ልጋ ላይ ተኝ​ተ​ዋል፤ እሰ​ጥህ ዘንድ መነ​ሣት አል​ች​ልም’ ይለ​ዋ​ልን? ወዳጁ ስለ​ሆነ ሊሰ​ጠው ባይ​ነሣ እንኳ እን​ዳ​ይ​ዘ​በ​ዝ​በው ተነ​ሥቶ የወ​ደ​ደ​ውን ያህል ይሰ​ጠ​ዋል። እኔም እላ​ች​ኋ​ለሁ፦ ለምኑ፥ ይሰ​ጣ​ች​ኋ​ልም፤ ፈልጉ፥ ታገ​ኛ​ላ​ች​ሁም፤ ደጅ ምቱ፥ ይከ​ፈ​ት​ላ​ች​ኋ​ልም። የሚ​ለ​ምን ሁሉ ይሰ​ጠ​ዋ​ልና፤ የሚ​ፈ​ል​ግም ያገ​ኛ​ልና፤ ደጅ ለሚ​መ​ታም ይከ​ፈ​ት​ለ​ታ​ልና። ከእ​ና​ንተ መካ​ከል ልጁ ዳቦ የሚ​ለ​ም​ነው አባት ቢኖር ድን​ጋይ ይሰ​ጠ​ዋ​ልን? ዓሣ ቢለ​ም​ነ​ውስ በዓሣ ፋንታ እባ​ብን ይሰ​ጠ​ዋ​ልን? ወይስ ዕን​ቍ​ላል ቢለ​ም​ነው በዕ​ን​ቍ​ላል ፋንታ ጊንጥ ይሰ​ጠ​ዋ​ልን? እና​ንተ ክፉ​ዎች ስት​ሆኑ ለል​ጆ​ቻ​ችሁ መል​ካም ስጦ​ታን መስ​ጠ​ትን የም​ታ​ውቁ ከሆነ፥ የሰ​ማይ አባ​ታ​ች​ሁማ ለሚ​ለ​ም​ኑት መል​ካ​ሙን ሀብተ መን​ፈስ ቅዱስ እን​ዴት አብ​ዝቶ ይሰ​ጣ​ቸው ይሆን?”