አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም ባበቃ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው፥ አንተም እኛን መጸለይ አስተምረን!” አለው። ኢየሱስም “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ አላቸው፤ ‘[በሰማይ የምትኖር] አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ! መንግሥትህ ትምጣ! የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን! እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥ በደላችንን ይቅር በልልን፤ ወደ ፈተናም አታግባን’ [ከክፉ አድነን እንጂ።]” ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ለምሳሌ ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ኖሮት፥ ያ ወዳጁ በእኩለ ሌሊት ወደዚያ ወደ ወዳጁ ቤት ሄዶ፥ ‘ወዳጄ ሆይ፥ እባክህ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ ወዳጄ የሆነ አንድ ሰው ከሩቅ መንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ምግብ የለኝም!’ ቢለው ታዲያ፥ ያ ወዳጁ ከውስጥ ሆኖ፥ ‘እባክህ አታስቸግረኝ! በሩ ተቈልፎአል፤ ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ተኝተዋል፤ ስለዚህ ተነሥቼ የፈለግኸውን እንጀራ ልሰጥህ አልችልም፤’ ይለዋልን? ምንም እንኳ ስለ ወዳጅነቱ ተነሥቶ ሊሰጠው ባይፈልግ ስለ ነዘነዘው ተነሥቶ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል እላችኋለሁ። “ስለዚህ እኔም እናንተን የምላችሁ ይህን ነው፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። ከእናንተስ አባት ሆኖ፥ ልጁ [ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማን ነው?] ዓሣስ ቢለምነው በዓሣ ፈንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠትን ካወቃችሁ በሰማይ የሚኖር አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!”
የሉቃስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 11:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች