ሉቃስ 11:1-13
ሉቃስ 11:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ በአንዲት ቦታ ጸለየ፤ ጸሎቱን በጨረሰ ጊዜም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ አስተማራቸው ጸሎት አስተምረን” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን። የዕለት ምግባችንን በየዕለቱ ስጠን። እኛም የበደለንን ሁሉ ይቅር እንድንል በደላችንን ይቅር በለን፤ አቤቱ፥ ወደ ፈተና አታግባን፤ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ።” እንዲህም አላቸው፥ “ከመካከላችሁ ወዳጅ ያለው ሰው ቢኖር በመንፈቀ ሌሊትም ወደ እርሱ ሄዶ እንዲህ ቢለው፦ ‘ወዳጄ ሆይ ሦስት እንጀራ አበድረኝ። ወዳጄ ከመንገድ መጥቶብኛልና የማቀርብለት የለኝም።’ ያ ወዳጁም ከውስጥ ሆኖ፦ ‘አትዘብዝበኝ፤ ደጁን አጥብቀን ዘግተናል፤ ልጆችም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ተኝተዋል፤ እሰጥህ ዘንድ መነሣት አልችልም’ ይለዋልን? ወዳጁ ስለሆነ ሊሰጠው ባይነሣ እንኳ እንዳይዘበዝበው ተነሥቶ የወደደውን ያህል ይሰጠዋል። እኔም እላችኋለሁ፦ ለምኑ፥ ይሰጣችኋልም፤ ፈልጉ፥ ታገኛላችሁም፤ ደጅ ምቱ፥ ይከፈትላችኋልም። የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤ የሚፈልግም ያገኛልና፤ ደጅ ለሚመታም ይከፈትለታልና። ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ የሚለምነው አባት ቢኖር ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ቢለምነውስ በዓሣ ፋንታ እባብን ይሰጠዋልን? ወይስ ዕንቍላል ቢለምነው በዕንቍላል ፋንታ ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠትን የምታውቁ ከሆነ፥ የሰማይ አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካሙን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንዴት አብዝቶ ይሰጣቸው ይሆን?”
ሉቃስ 11:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም እንደ ጨረሰ፣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “ጌታ ሆይ፤ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው አንተም መጸለይን አስተምረን” አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፤ “ ‘አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ የዕለት እንጀራችንን በየዕለቱ ስጠን፤ በደላችንን ይቅር በለን፤ እኛም የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና። ወደ ፈተናም አታግባን፤ ከክፉው አድነን እንጂ።’ ” ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ቢኖረውና በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ፣ ‘ወዳጄ ሆይ፤ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ አንድ ባልንጀራዬ ከመንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ነገር የለኝምና’ ብሎ ለመነው እንበል። በቤት ውስጥ ያለውም፣ ‘አታስቸግረኝ፤ በሩ ተቈልፏል፤ ልጆቼም ዐብረውኝ ተኝተዋል፤ ከእንግዲህ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም’ ይለዋልን? እላችኋለሁ፤ ወዳጁ በመሆኑ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፣ ስለ ንዝነዛው ብቻ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። “ከእናንተ መካከል አባት ሆኖ ሳለ ልጁ ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጠው ይኖራልን? ወይስ ዕንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ በሰማይ ያለው አባት ታዲያ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጥ?”
ሉቃስ 11:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን። እንዲሁም አላቸው፦ ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ አለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? ያም ከውስጥ መልሶ፦ አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። እኔም እላችኋለሁ፦ ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችሁማል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?
ሉቃስ 11:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን ኢየሱስ በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ ጸሎቱንም ባበቃ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት እንዳስተማራቸው፥ አንተም እኛን መጸለይ አስተምረን!” አለው። ኢየሱስም “ስትጸልዩ እንዲህ በሉ አላቸው፤ ‘[በሰማይ የምትኖር] አባታችን ሆይ! ስምህ ይቀደስ! መንግሥትህ ትምጣ! የዕለት እንጀራችንን በየቀኑ ስጠን! እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥ በደላችንን ይቅር በልልን፤ ወደ ፈተናም አታግባን’ [ከክፉ አድነን እንጂ።]” ቀጥሎም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ለምሳሌ ከእናንተ አንዱ ወዳጅ ኖሮት፥ ያ ወዳጁ በእኩለ ሌሊት ወደዚያ ወደ ወዳጁ ቤት ሄዶ፥ ‘ወዳጄ ሆይ፥ እባክህ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ ወዳጄ የሆነ አንድ ሰው ከሩቅ መንገድ መጥቶብኝ የማቀርብለት ምንም ምግብ የለኝም!’ ቢለው ታዲያ፥ ያ ወዳጁ ከውስጥ ሆኖ፥ ‘እባክህ አታስቸግረኝ! በሩ ተቈልፎአል፤ ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ተኝተዋል፤ ስለዚህ ተነሥቼ የፈለግኸውን እንጀራ ልሰጥህ አልችልም፤’ ይለዋልን? ምንም እንኳ ስለ ወዳጅነቱ ተነሥቶ ሊሰጠው ባይፈልግ ስለ ነዘነዘው ተነሥቶ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል እላችኋለሁ። “ስለዚህ እኔም እናንተን የምላችሁ ይህን ነው፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። ከእናንተስ አባት ሆኖ፥ ልጁ [ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማን ነው?] ዓሣስ ቢለምነው በዓሣ ፈንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ ዕንቊላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠትን ካወቃችሁ በሰማይ የሚኖር አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!”
ሉቃስ 11:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፤ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “ጌታ ሆይ! ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንዲሁ መጸለይን አስተምረን፤” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በማናቸውም ጊዜ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባት ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በለን፤ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር እንላለንና፤ ወደ ፈተናም አታግባን።’ ” እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ ማን ይሆን ወዳጅ ኖሮት፥ በእኩለ ሌሊት ወደ እርሱ ሄዶ እንዲህ የሚለው፦ ‘ወዳጄ ሆይ! ሦስት እንጀራ አበድረኝ፤ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት ምንም የለኝምና’፤ ያም ከውስጥ መልሶ፦ ‘አታስቸግረኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ ናቸው፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም፤’? እላችኋለሁ፤ ወዳጁ ስለ ሆነ እንኳ ተነሥቶ ባይሰጠው፥ ስለ ንዝነዛው ግን ተነሥቶ የሚፈልገውን ያህል ይሰጠዋል። እኔም እላችኋለሁ፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ ዓሣ ቢለምነው፥ በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንግዲያውስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው!”