ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሣቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ዘለለ፤ በኤልሣቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት። በታላቅ ቃልም ጮሃ እንዲህ አለች፥ “ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ? እነሆ፥ ሰላምታ ስትሰጭኝ ቃልሽን በሰማሁ ጊዜ፥ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽ ቃል እንደሚሆን የምታምኚ አንቺ ብፅዕት ነሽ።” ማርያምም እንዲህ አለች፥ “ሰውነቴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች። ልቡናዬም በአምላኬ በመድኀኒቴ ሐሤት ታደርጋለች። የባርያውን ትሕትና ተመልክቶአልና። እነሆ፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል። ታላቅ ሥራን ሠርቶልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ይቅርታውም ለሚፈሩት ለልጅ ልጅ ነው። በክንዱ ኀይልን አደረገ፤ በልባቸው ዐሳብ የሚታበዩትንም በተናቸው። ኀያላኑን ከዙፋናቸው አዋረዳቸው፤ ትሑታኑንም ከፍ ከፍ አደረጋቸው። የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው፤ ባለጠጎችንም ባዶ እጃቸውን ሰደዳቸው። ብላቴናውን እስራኤልን ተቀበለው፤ ይቅርታውንም ዐሰበ። ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ እስከ ዘለዓለም እንደ ተናገረው።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች፤ ከዚህ በኋላም ወደ ቤቷ ተመለሰች። የኤልሣቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ዘመዶችዋና ጎረቤቶችዋም እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። ከዚህም በኋላ በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገዝሩት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን መልሳ፥ “አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ” አለች። እነርሱም፥ “ከዘመዶችሽ ስሙ እንደዚህ የሚባል የለም” አሉአት። አባቱንም ጠቅሰው፥ “ማን ሊሉት ትወዳለህ?” አሉት። ብራናም ለመነና “ስሙ ዮሐንስ ይባል” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተናገረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ። በዚያም ሀገር ሰው ሁሉ ላይ ፍርሀት ሆነ፤ ይህም ነገር ሁሉ በይሁዳ በተራራማው ሀገር ሁሉ ተወራ። የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና። በአባቱ በዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ መላበት፤ እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረ፦ “ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን በነቢያት አፍ እንደ ተናገረ። ከጠላቶቻችን እጅ፥ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ። ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ፥ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ። ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ያስብ ዘንድ። ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሀት፥ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ በዘመናችን ሁሉ እንድናመልከው ይሰጠን ዘንድ። አንተም ሕፃን፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ትጠርግ ዘንድ በፊቱ ትሄዳለህና። ኀጢአታቸው ይሰረይላቸው ዘንድ መድኀኒታቸውን እንዲያውቁ ለአሕዛብ ትሰጣቸው ዘንድ። ከአርያም በጐበኘን በአምላካችን በይቅርታውና በቸርነቱ። በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩት ብርሃኑን ያሳያቸው ዘንድ፥ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ።” ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸና፤ ለእስራኤልም እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:40-80
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች