ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት። ማርያምም እንዲህ አለች፦ ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው። ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል። ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል። ማርያምም ሦስት ወር የሚያህል በእርስዋ ዘንድ ተቀመጠች ወደ ቤትዋም ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፥ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ወደዱ። እናቱ ግን መልሳ፦ አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ አለች። እነርሱም፦ ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም አሉአት። አባቱንም ማን ሊባል እንዲወድ ጠቀሱት። ብራናም ለምኖ፦ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም እየባረከ ተናገረ። ለጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በይሁዳ በተራራማው አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፦ እንኪያ ይህ ሕፃን ምን ይሆን? እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ፦ የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:40-80
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos