በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስሟ ናዝሬት ወደምትባለው ወደ አንዲት የገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሚሆን ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨችው ወደ አንዲት ድንግል ተላከ፤ የዚያችም ድንግል ስምዋ ማርያም ይባል ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፥ “ደስ ያለሽ፥ ጸጋንም የተመላሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። እርስዋም በአየችው ጊዜ ከአነጋገሩ የተነሣ ደነገጠችና “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?” ብላ ዐሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፥ “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱም ታላቅ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል። ለያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለሙ ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፥ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፥ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል። እነሆ፥ ከዘመዶችሽ ወገን የምትሆን ኤልሣቤጥም እርስዋ እንኳ በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ፀንሳለች፤ መካን ትባል የነበረችው ከፀነሰች እነሆ፥ ይህ ስድስተኛ ወር ነው። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና”። ማርያምም መልአኩን፥ “እነሆኝ፥ የእግዚአብሔር ባሪያው አለሁ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለችው፤ ከዚህ በኋላም መልአኩ ከእርስዋ ዘንድ ሄደ። በዚያም ወራት ማርያም ፈጥና ተነሣች፤ ወደ ተራራማው ሀገር ወደ ይሁዳ ከተማም ደረሰች። ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሣቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ዘለለ፤ በኤልሣቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት። በታላቅ ቃልም ጮሃ እንዲህ አለች፥ “ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ? እነሆ፥ ሰላምታ ስትሰጭኝ ቃልሽን በሰማሁ ጊዜ፥ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከእግዚአብሔር ዘንድ የነገሩሽ ቃል እንደሚሆን የምታምኚ አንቺ ብፅዕት ነሽ።”
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 1
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:26-45
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos